የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች አልሸባብን በመደምሰስ አኩርተውናል-የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች

99

ነሐሴ 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች አልሸባብን በመደምሰስ አኩርተውናል ሲሉ በሱማሌ ክልል የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የአካባቢያቸውን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች የፌደራልና የሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች አሸባሪውን የአልሸባብ ቡድን በመደምሰስ የሀገርን ዳር ድንበር በማስከበራቸው ያለስጋት ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ አልሸባብ ኢትዮጵያን ከምኞት አልፎ ማተራመስ እንደማይችል በወሰደው የማያዳግም ርምጃ ስላረጋገጠ ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አብዲ ሁሴን እና ዳናዊት ኃይሌ አልሸባብ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እያለ ግን መቼም አይሳካለትም ይላሉ።

የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ በአልሸባብ ላይ የወሰደው ርምጃ እጅግ እንዳኮራቸው ገልጸው፤ርምጃው ዜጎች ያለስጋት በሰላም ወጥተው እንዲገቡ አድርጓል ብለዋል።

የከተማዋ ወጣቶችና ህብረተሰቡም ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት ለከተማዋ ሰላም እየተጉ መሆኑን ነው የገለጹት።

አስፈላጊውን ፍተሻ በማድረግና ጸጉረ ልውጦችን በማጋለጥ ለሀገራቸው ሰላምና ደህንነት መከበር እየሰሩ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዩሱፍ መሐመድ፣አቶ ወገን ገለታ እና ወጣት ተስፋየ ብርሃኑ የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ በሽብር ቡድኑ ላይ የወሰዱት ርምጃ የቡድኑን ዕኩይ ዓላማ ያከሸፈ የሚያስደንቅ ርምጃ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ህዝቡ በአልሸባብ እንጠቃለን ከሚል ስጋት መውጣቱን፣ ከተማዋም ካለምንም ስጋት በሰላምና በመረጋጋት መደበኛ እንቅስቃሴዋን እየከወነች መሆኑን አንስተዋል።

የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች በየቀበሌው በመደራጀት በንቃት አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆኑንና ከፀጥታ ኃይሉ ጋርም በፍጥነት መረጃ እንደሚለዋወጡ ጠቁመዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ለፀጥታ ኃይሉ ሲያደርጉ የቆዩት የሞራልና የስንቅ ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

የጎዴ ከተማ አስተዳድር የፀጥታ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሺ አብዲ በበኩላቸው የከተማዋ ነዋሪ አልሸባብን እየተዋጋ ለነበረው ሠራዊት ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አረጋግጠዋል።

ሕብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በንቃት መጠበቁም የአልሸባብ የሽብር ቡድን በጎረቤት አገራት የሚፈጽማቸው ዕኩይ ተግባራት በኢትዮጵያ እንዳይደገሙ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የፀጥታ ኃይሉና የከተማዋ ነዋሪ እጅና ጓንት በመሆን ፀጉረ ልውጦችን የማጋለጥና በቁጥጥር ስር የማዋል ርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም