ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ከማዘመን ጎን ለጎን ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ

171

ነሀሴ 01/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ 'አርዳይታ' ምርጥ ዘር እርሻ ልማት አካባቢ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለትምህርት ቤት ማስፋፊያና ለኤሌክትሪክ ማስገቢያ የሚውል 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ከዚህ ቀደምም አሰላ፣ ኮፈሌና አርዳይታ አከባቢ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤቶችን አስገንብቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ድጋፉን ለአካባቢው አገር ሽማግሌዎች ያስረከበቡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክፍሌ ወልደማርያም እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን፣ የእርሻ መሳሪያዎችን የሚያቀርብ ሲሆን የሜካናይዜሽን አገልግሎትንም ይሰጣል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ ከማቀርብ በተጓዳኝ ማህበራዊ ኋላፊነቱንም እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለ"ወልተኢ" ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያና ለ"ወልተኢ" ቀበሌ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስገቢያ የሚውል 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

የገደብ አሳሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወል ወልዩ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ለህዝብ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ድጋፍ በማድረግ የህዝብ ድርጅት መሆኑን አሳይቷል ብለዋል፡፡

የአካባቢው ማህበረሰብም የኮርፖሬሽኑን የምርጥ ዘር ቡቃያና ሌሎች ንብረቶቹ እንደ ራሱ ንበረት ሊጠብቅና ሊንከባከብ ይገባለም ብለዋል፡፡

የአከባቢው የአገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎችም ኮርፖሬሽኑ ህዝቡ ብርሃን እንዲያገኝና ልጆጃቸው በቅርበት እንዲማሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅረበዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሰራተኞች በአርዳይታ ምርጥ ዘር እርሻ ልማት ቅጥር ግቢ ውስጥ የአርንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ 25 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትና ጣቢያዎች ያሉት የመንግስት የልማት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም