በከተማ የምግብ ዋስትና የሚረጋገጠው በዘርፉ የተጀመረው ግብርና በእያንዳንዱ ነዋሪ ዘንድ መድረስ ሲችል ነው

121

መቂ ነሀሴ 01/2014(ኢዜአ)በከተማ የምግብ ዋስትናን ማረጋጥ የምንችለው በከተሞች የጀመርነውን ግብርና በእያንዳንዱ ነዋሪ ዘንድ ማድረስ ስንችል ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

ፕሬዘዳንቱ በምስራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ የከተማ ግብርና የስራ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝተዋል።

አቶ ሽመልስ በወቅትቱ እንደገለፁት የክልሉ መንግስት በአዲሱ 2015 የበጀት ዓመት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ጅምር ላይ ያለውን የከተማ ግብርና አጠናክሮ ማስቀጠል ነው ።

"የከተማ ነዋሪዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የከተማ ግብርና ቁልፍ ሚና አለው" ያሉት አቶ ሽመልስ "ይሄን ማድረግ የምንችለው ፕሮግራሙን በእያንዳንዱ የከተማ ነዋሪ ዘንድ ስንተገብር ነው" ብለዋል ።

"በአዲሱ በጀት ዓመት በልዩ ንቅናቄ ስራውን ለማከናወን እየሰራን ነው"  ሲሉ አስታውቀዋል ።

አቶ ሽመልስ ከከተማ ግብርናው በተጨማሪ የዱግዳና ቦራ ወረዳ ሞዴል አርሶ አደሮች በመቂ ከተማ እያስገነቡ ያለውን የመኖሪያ መንደር ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው "በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን እያረጋገጥን መሆኑን በአርሶ አደሮቹ እየተገነቡ ያሉት ዘመናዊ ቤቶች ማሳያ ናቸው"  ብለዋል ።

የኦሮሚያ ከተሞች ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው በክልሉ በ700 ከተሞች በ40 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ መሆኑን ተናግሯል ።

በልማቱ ከ110 ሺህ በላይ የከተማ ነዋሪዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው እስከ አሁን 32 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ካሮት፣ ቆስጣ፣ የሃበሻ ጎመንና ቀይ ስር የአትክልት አይነቶች እየለሙ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

በተመሳሳይ የወተት ላሞችና የዶሮ እርባታ እንዲሁም የበግና ፍየሎች እርባታና ማድለብና ንብ ማነብ፣ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። ።

"በከተሞቹ እየተከናወኑ ባሉ የግብርና ስራዎች የከተማ ነዋሪዎችን የምግብ ዋስትና በሂደት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት ለመጣል ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው" ብለዋል ።

በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 3ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረውን የከተማ ግብርና ስራን በ2015 የበጀት ዓመት ወደ 40ሺህ ሄክታር በማሳደግ ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል  ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም