ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት አመት 11 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከሰጠው ብድር መሰብሰቡን ገለጸ

127

ነሀሴ 01/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተጠናቀቀው 2014 በጀት አመት 10 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ከሰጠው ብድር መሰብሰብ መቻሉን ገለፀ።

ባንኩ የትግራይ ክልል ፕሮጀክቶችን ሳይጨምር የተበላሸ ብድር ደረጃን ወደ 17 በመቶ ማውረድ መቻሉንም አስታውቋል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት በትግራይ ያሉ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ተበላሸ ብድር መግባታቸው አመቱን ለባንኩ ፈታኝ አድርጎታል።

ባንኩ የገጠመውን ችግር ለማካካስ ፈጣን ለውጦችን ማድረግ በመቻሉ ትግራይን ሳይጨምር በ2013 ዓ.ም የነበረውን የተበላሸ የብድር ደረጃ ከነበረበት 15 ቢሊዮን ብር በበጀት አመቱ ወደ 9 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።        

ባንኩ 11 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከብድር መሰብሰቡን ጠቅሰው በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን ገልፀዋል።

ባንኩ በብድር አሰባሰብ ላይ የጀመረውን ስራ በማጠናከር በተያዘው 2015 በጀት አመት 14 ቢሊዮን ብር ከብድር ለመሰብሰብ ማቀዱንም አስረድተዋል።

የተበላሸ ብድር ደረጃን በ2014 በጀት አመት ከነበረበት 17 በመቶ በተያዘው በጀት አመት ወደ 10 በመቶ ለማውረድ መታቀዱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም