የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ከደለል ለመታደግ 100 ሺህ ሄክታር ተራራማ ስፍራን ማልማት ይጠይቃል -ምሁራን

154

አርባ ምንጭ ሐምሌ 30/2014 (ኢዜአ) የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ከደለል መሞላት ለመታደግ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሸፍን የጋሞ ዞን ተራራማ ስፍራዎችን በችግኝ የማልበስና የማልማት ስራ እንደሚጠይቅ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታወቁ ፡፡

የአሁኑ ትውልድ ሀይቆቹን የማዳን ሃላፊነቱን በአግባቡ ካልተወጣ እስከ መጨረሻው ሊጠፉ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን ምሁራኑ አመላክተዋል ።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ስነ-ምህዳር  ተመራማሪ  ዶክተር ፋሲል  እሸቱ  ለኢዜአ እንደገለጽት በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች መካከል ትልልቆቹ የሆኑት አባያና ጫሞ በደለል አፈር እየተሞሉ ህልውናቸው አደጋ ላይ  መውደቁ በጥናት ተረጋግጧል፡፡

በሀይቆቹ ራስጌ የሚገኙ የጋሞ ዞን ሰንሰለታማ ተራሮች ባለመልማታቸው በየዓመቱ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን በላይ ደለል አፈር ወደ ጫሞ ሀይቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ወደ አባያ ሀይቅ የሚገባው ደለል አፈር ደግሞ የእጥፍ ያክል እንደሚሆን አመልክተዋል።

"የሀይቆቹ በደለል መሞላት ለእንቦጭ አረም መስፋፋት አመቺ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ የሀይቆቹን የምግብ ሰንሰለት በእጅጉ የጎዳ በመሆኑ በዓሣ ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል" ፡፡

ሀይቆቹን ለማዳን በጋሞ ዞን 10 ወረዳዎችን የሚያካልል ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ ተራራማ መሬትን ማልማት እንደሚገባ ጠቁመው ተራሮቹን ለማልማት ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ እንደሚፈጅ አመልክተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀይቆቹ ዙሪያ ያደረገው ጥናት ዓለም አቀፍ እውቅና በማግኘቱ የጀርመን መንግስት ወጪውን ለመሸፈን ቃል መግባቱን ጠቅሰው ለተፈጻሚነቱ የመንግስትና ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመዋል፡፡

"ይህ ትውልድ ሀይቆቹን ለማዳን የመጨረሻ ትውልድ ነው" ያሉት ዶክተር ፋሲል የሀይቆቹን ደህንነት ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሀይቆች ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙት አፈርና ማዳበሪያ በዝናብ አማካኝነት ታጥቦ ወደ ሀይቆቹ  መግባት ለእንቦጭ አረም መስፋፋት ዋንኛ ምክንያት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዉሃ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ምክትል ዳይሬክተርና ተመራማሪ ዶክተር ደመላሽ ወንድማገኘው ናቸው፡፡

ደለል አፈርና እንቦጭ አረም በሀይቆቹ መጠን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ ከሀይቆቹ ውስጥ በሚገኙ ዓሳና ሌሎች ምርቶች ላይም አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ሀብት የሆኑ ሀይቆችን በደለል ምክንያት እንዳናጣቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሠሩ እንደምገባ አስገንዝበዋል፡፡

በጋሞ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽህፈት ቤት የብዝሀ ህይወት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የብዝሃ ህይወት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጋንቡራ ጋንታ በበኩላቸው የደን መመናመን ለችግሩ መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በሰው ሰራሽ ችግር፣ በመሬት መንሸራተትና በጎርፍ አደጋዎች የበርካታ ሰው ህይወትና ንብረት ላይ የተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸውን አንስተዋል ፡፡

በዚሁ ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት በክረምት ዝናብ ምክንያት በተፈጠረ ጎርፍና ናዳ የተፈናቀሉ 2 ሺህ 513 የቤተሰብ አባላት ያሏቸዉ 360 አባወራዎች መኖራቸውን ለአብነት አንስተዋል ፡፡

ተጎጂዎችን ወደሌላ አከባቢ አዛውሮ በማስፈር በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው አካባቢው  ላይ አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ማከናወም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ማጠናከር የግድ የሚል ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት በሀይቆቹ ዙሪያ ያሉ ተራሮችን ችግኝ የማልበስ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት መሠረት የጋሞ ዞን ተራራማ አካባቢዎችን በተፋሰስ ልማት መሸፈን ሀይቆችን ከመታደግም በላይ የዞኑን ህዝብ ህልውና ማስጠበቅ በመሆኑ ተቋማቸው ለተፈጻሚነቱ በባለቤትነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አቶ ጋንቡራ አስረድተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም