የከተማ ግብርና ልማት መጠናከር ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል---የስነ ምግብ ምሁራን

324

ሀዋሳ (ኢዜአ) ሐምሌ30/2014 የከተማ ግብርና ልማት ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን በማሳደግ አምራች ትውልድ ስለሚፈጥር ሥራውን በምርምር መደገፍ ይገባል ሲሉ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የስነ ምግብ ምሁራን ገለጹ።

የስነ ምግብ መምህራንና ተመራማሪዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ መንግስት በከተማ ግብርና ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ማህበረሰቡን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

በኮሌጁ የስነ ምግብ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ረታ እንደሚሉት "በተለይ በከተማ በትንሽ መሬት ላይ የሚከናወነው የግብርና ልማት ሥራ ኢኮኖሚን ከመደገፍ ባለፈ ጤናማ ማህበረሰብ እንዲፈጠር አበርክቶው የጎላ ነው" ብለዋል።

የከተማ ግብርና ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን በማጎልበት ጤናው የተጠበቀ አምራች ትውልድ እንዲፈጠር የሚያግዝ መሆኑንም ነው መምህርና ተመራማሪው የገለጹት።

"በመሆኑም መንግስት በትኩረት እያከናወነ ያለውን ሥራ በምርምር መደገፍና ቀጣይነት እንዲኖረው ማገዝ ያስፈልጋል" ብለዋል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ፣ በከተማ ማህበረሰብ የምግብ ብቻ ሳይሆን የጤና ችግርም ስለሚስተዋል የከተማ ግብርናው ከምግብ ባለፈ የአካል እንቅስቃሴ ለማድረግ ዕድል ስለሚፈጥር ጠቀሜታው የጎላ ነው ።

ህብረተሰቡን ከተፈጥሮ ጋር በማዛመድ ጭንቀትን ጨምሮ የደም ግፊት፣ ስኳርና ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

"እንደ ሃገር መንግስትም ለሥራው ትኩረት መስጠቱ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ስለሚያሳድግ ልማቱን ውጤታማ ያደርገዋል" ብለዋል።  

ዜጎች ከዚህ ልምድ ወስደው ባላቸው መሬት ላይ ልማቱን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ነው ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ያመለከቱት።

በከተማ ግብርና የሚለማው ተፈጥሯዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ስለሆነ ጤናማ ሕይወትን ለመምራት አጋዥ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኮሌጁ የስነ ምግብ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርት ሃዊ ተስፋዬ ናቸው።

ቶሎ የሚደርሱና በየጊዜው ለምግብት የሚውሉ የተለያዩ አትክልቶችን አልምቶ በብዛት መመገብ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል በኩል ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከተማ ግብርና ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚገልጹት መምህርት ሃዊ፣ "የምንኖርበት አካባቢ አረንጓዴ መሆን ለአዕምሮ ጤናም ጉልህ ድርሻ አለው" ይላሉ።

ህብረተሰቡ የከተማ ግበርናን ልማድ አድርጎት እንዲቀጥል ደግሞ ከዘር አቅርቦት ጀምሮ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና ግንዛቤ የማሳደግ ስራን ተከታታይነት ባለው መልኩ ማጠናከር እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የከተማ ግብርና ጤናማና ደስተኛ ሕይወት ለመምራት እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ የተመረቀችው ወጣት ኬሪያ ሃቢብ በበኩሏ እንዳለቸው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጠባብ ግቢ የጀመረችው የአትክልት ልማት የምግብ ፍጆታዋን እንድትሸፍን አስችሏታል።

የውሃ ላስቲኮችና ሌሎች ያገለገሉ እቃዎችን በመጠቀም ካሮት፣ ጎመን፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ቃሪያና መሰል አትክልቶችን በማልማት ቤተሰቦቿንና አካባቢዋን ተጠቃሚ ማድረጓን ትገልጻለች፡፡

በቀላሉ በግቢዋ በምታለማው አትክልት የምግብ ወጪዋን ከመሸፈን ባለፈ ጤናማ ሕይወት ለመምራት እንዳስቻላት ተናግራለች፡፡

ወጣት ኬሪያ እንዳለችው የከተማ ግብርና እንደሀገር ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ልማቱን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማገዝ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሁሉም ከተሞች የከተማ ግብርና ልማት ሥራ እየተለመደ መምጣቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም