የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ የምርኮኞች አያያዝን የተከተለና ርህራሄ የተሞላበት እንክብካቤ እያደረገልን ነው- የተማረኩ የአልሸባብ አባላት

161

ሐምሌ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ የምርኮኞች አያያዝን የተከተለና ርህራሄ የተሞላበት እንክብካቤ እያደረገላቸው መሆኑን የተማረኩ የአልሸባብ ሽብር ቡድን አባላት ተናገሩ።

በምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የአልሸባብ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያ ጸጥታ ኃይሎች ተደምስሷል።

የሽብር ቡድኑ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ታጣቂዎች በመከላከያ ሰራዊት እና በሶማሌ ክልል ጸጥታ ኃይል በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ምርኮኞች መካከል ከዘጠኝ ወር በፊት ቡድኑን የተቀላቀለው አብዱላሂ ሀሰን አብዲ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ተልዕኮ በመቀበል ጥቃት ለመፈጸም ባደረጉት ሙከራ ወቅት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጿል።

በኮህሌ ወረዳ ሕዝብ ውስጥ ሰርጎ ገብቶ የተያዘው አብዱላሂ ጀማል ሮብሌ እና በድኑን ከአምስት ዓመታት በፊት የተቀላቀለው አያልኔ መሐመድ አህመድ የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ እጅ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሽብር ተልዕኮ ይዘው ቢመጡም ባልጠበቁት መልኩ ቢማረኩም የኢትዮጵያ መንግሥት  ዓለም አቀፍ የምርኮኛ አያያዝን በተከተለ አግባብ እንክብካቤ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በቁጥጥር ሥር ከዋልን በፀጥታ ኃይሉ እንገደላለን የሚል ስጋት እንደነበራቸው ጠቅሰው፤ የጠበቃቸው ግን በተቃራኒው ፍጹም ርህራሄ የተሞላበት የምርኮኛ አያያዝ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለቀናት በረሃብና በውሃ ጥም ቢቆዩም የኢትዮጵያ ጸጥታ ኃይሎች የተራቡትን አብልቶ፣ የታረዙትን አልብሶና የታመሙትን እያሳከመ፣ የንጽህና ግብዓቶችን እያሟላ በጥሩ እንክብካቤ እንደያዛቸው ነው ያረጋገጡት።

በጸጥታ ኃይሉ ሥር በመሆናቸውም ምንም አይነት ስጋት እንደሌላቸው ነው የተናገሩት።

የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊና የጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሜጀር ጄነራል ተስፋዬ አያሌው እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል መሃመድ አህመድ ምርኮኞችን በአግባቡ መያዛቸውን አረጋግጠዋል።

የአሸባሪው ቡድን አባላት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሰርገው ቢገቡም የኢትዮጵያ መከላከያና የክልሉ ልዩ ኃይል ወታደራዊ ዲሲፒሊን ያላቸው በመሆኑ ዓለም አቀፍ ምርኮኛ አያያዝን ደንብን በጠበቀ አግባብ እንደተያዙ ገልጸዋል።

በዚህም በጸጥታ ኃይሉ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ከ100 በላይ ምርኮኞች ሰብዓዊነት በተሞላበት አግባብ እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም