ወደ ውጪ ከተላኩ ምርቶች ከ31 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ተገኘ

234

ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 29/2014 (ኢዜአ)፡ በኢንተርፕራይዞች ልማት ተመርተው ወደ ውጪ ከተላኩ ምርቶች ከ31 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንተር ፕራይዞች ልማት አስታወቀ።

የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተር ፕራይዝ የፋይናስ ፕሮጀክት ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ወልዴ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ኢንተርፕራይዞች  ምርቶቻቸው በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ  የሚሰጣቸው ስልጠና ውጤታማ እያደረጋቸው ነው።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት አመት ኢንተርፕራይዞች እሴት በመጨመር የማር፣ ዕጣንና ሙጫ፣ አልባሳት የቆዳ ውጤቶችን ጨምሮ 10 ሚሊየን ኪሎ ግራም ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻላቸውን አስረድተዋል።

እሴት በመጨመር ከላኩት ምርትም 31 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን አስረድተዋል።

 በ2015 ዓ.ም በጀት አመት ወደ ውጪ ከሚላኩ ምርቶች 18 ሚሊየን ኪሎ ግራም እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በመላክ 37 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማስገኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የክህሎት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም የሀገሪቱን እንድገት ለማፋጠን በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

 የማምረቻ ማሽን ፋይናስ ግዥ አገልግሎቶች እንደሚጠናከሩ አመልክተው፤ የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚካሄደው ምክክር ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

 የአነስተኛ እና መካካለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሮ የመንዝወርቅ ግርፌ  ኢንተርፕራይዞችን በገበያው ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ጊዜያት የዓለም ባንክ ተከታታይ ድጋፍ  ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ለቀጣይ አምስት ዓመት  የሚሆን 200 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ በጀት መመደቡንም ገልጸዋል።

 አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው አነስተኛና መካከለኛ እንተርፕራይዞች ድጋፈ እንሚያስፈልጋቸው የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል እንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ዮሐንስ አማረ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኢንተር ፕራይዝ ልማት 512 ለሚሆኑ ባለሙያዎችና ለ300 ኢንተር ፕራይዞች የስነልቦና ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን ጠቁመዋል።

 ኢንተር ፕራይዞቹ በጥራትና በስፋት አምርተው በሀገር ውስጥና በውጪ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ተገቢው የብድር አገልግሎት እንዲቀርብ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኩ  የአምራች ኢንተርፕራይዝ ሃላፊዎች እና ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎችም በደብር ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከአንድ ሺህ በላይ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ኢዜአ ከሥፍራው ዘግል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም