ህብረተሰቡ የአልጋ አጎበር ና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ የወባን በሽታ ሊከላከል ይገባል- ዶክተር ሊያ ታደሰ

79

ጋምቤላ፤ ሐምሌ29/2014(ኢዜአ) ህብረተሰቡ የአልጋ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀምና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ እየጨመረ ያለውን የወባ በሽታ ሊከላከል እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

ሚኒስትሯ የጋምቤላን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት፤ ካለው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃም የወባ በሽታ መጨሩን ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልልም እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ወባ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ሁሉ የበሽታው ስርጭት የጨመረበት ሁኔታ መኖሩን   ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡም የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀምና ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰሰ   እራሱን የመጠበቅ  ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል  ብለዋል ።

ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩትና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር በመከላከልም ሆነ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች የህክምና አገልግሎትን እንዲያገኙ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን  አስረድተዋል።

የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮድ ጋትዊች በበኩላቸው፤ በክልሉ የክረምቱን መግቢያ ተከትሎ ሊጨምር የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከል  በሁሉም ወረዳዎች የፀረ- ወባ ኬሚካል ርጭትና ሌሎች  ለመከላከል የሚያግዙ ስራዎች መከናወናቸው ተናግረዋል።

ሆኖም  የክረምቱን ወቅት ተከትሎ በክልሉ ስምንት ወረዳዎች የወባ በሽታ የስርጭት መጠን ቀደም ካሉት ዓመታት በእጥፍ መጨመሩን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የበሽታው ስርጭት መጠን በጨመረባቸው ወረዳዎች የህክምና አገልግሎቱን ከማጠናከሩ በተጓዳኝ  ህብረተሰቡ የአጎበር አጠቃቀም ልምዱን እንዲያሳድግ የንቅናቄ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የጋምቤላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሮን ጉኝ እንዳሉት፤ በቀን በመደበኛና በድንገተኛ ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡት ከ400 በላይ ታካሚዎች መካከል እስከ 70 መቶ የሚሆኑት በወባ በሽታ የተጠቁ ናቸው።

በሽታውን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች በተጠና መልኩ ተጠናከረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም