ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትፈርስ የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ ድንቅ ባህልና እሴት ያላት ታላቅ ሀገር ናት-ጀኔራል ካሣዬ ጨመዳ

111

ደሴ ፤ ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም (ኢዜአ) ''ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትፈርስ የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ ድንቅ ባህልና እሴት ያላት ታላቅ ሀገር ናት፤ አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን ለትውልድ ማሻገርና ትንሳኤዋን ማቅረብ ይገባናል ሲሉ ብርጋዴል ጀኔራል ካሣዬ ጨመዳ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር በበኩሉ የውጭ ጫናውን በማቃለል ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ብርጋዴል ጀነራል ካሣዬ ጨመዳ በመከላከያ ሰራዊት ከ20 ዓመት በላይ ሀገራቸውን በታማኝነት ያገለገሉ፣ 16ኛ ሰንጥቅ ክፍለ ጦርን በአዛዥነት በብቃት የመሩ የሀገር ባለውለታ ጀነራል ናቸው፡፡

ብርጋዴል ጀነራሉ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትፈርስ የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ ድንቅ ባህልና እሴት ያላት ታላቅ ሀገር ናት።

ኢትዮጵያን በየዘመን ምዕራፉ በውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች ለማፍረስና ለመበታተን በተደጋጋሚ ቢሰሩም በህዝቦቿ የጋራ ትግልና የተባበረ ክንድ ማክሸፍ መቻሉን አስታውሰዋል።

"አሁንም ኢትዮጵያ አንድነቷን የሚፈታተን ችግር ቢገጥማትም በአንድ ላይ ቆመን በኢትዮጵያዊነት የጀግንነት ታሪክ ሴራውን በቅርቡ ማክሸፍ እንችላለን" ብለዋል፡፡

"ወጣቱም በሐሰት ወሬ ሳይደናገር ከመንግስት ጎን ፀንቶ መቆምና የሀገሩን ዳር ድንበር አስከብሮ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደምና በአጥንቱ ጭምር ማስቀጠል ይኖርበታል" ሲሉም አሳስበዋል።

አሸባሪው ህወሓት እድሜ ልኩን በሰራው ግፍና በደል ሳይፀፀት አሁንም ሀገር ለማፍረስ በየቦታው እሳት እየጫረ መሆኑን ጠቁመው፤ "የሚለኩሰውን እሳት በጥበብ ማጥፋትና እራሱን እንዲለበልበው ማድረግ ይገባል" ብለዋል፡፡

''የኢትዮጵያ ታሪክ አሸናፊነት ነው" ያሉት ብርጋዴል ጀኔራሉ፤ "አሁን ላይ ፈተናው ቢበዛም ትንሳኤዋ ቅርብ ነው'' ብለዋል።

"ከገጠሙን ውስብስብ ችግሮች ፈጥኖ ለመውጣት የጠላትን ሴራ በማክሸፍ አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን ሃገራችን ሳትደፈር ለትውልድ ለማሻገር ከእያንዳንዳችን ብርቱ ስራ ይጠበቃል" ሲሉ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ እንድሪስ መሃመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ከገጠማት መልከ ብዙ ችግር ለመታደግና ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት ዳያስፖራው የድርሻውን ይወጣል፣ እየተወጣም ነው ብለዋል፡፡

በተለያዩ የውጭ ሃገራት ከ5 ሚሊዮን በላይ ዲያስፖራ ይኖራል ተብሎ እንደሚታመን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስውን የውጭ ጫና ለማቃለል በተለያዩ የውጭ ሀገራት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

"በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በየደረጃው እየሰራን ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ "በተለይ የጤናና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረን ድጋፍ እያደረግን ነው" ብለዋል፡፡

ከመካከላችን በወጡ የስልጣን ጥመኞች ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ወግነው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርጉትን መፍጨርጨር ተጋግዘን በጋራ ሴራቸውን እናከሽፋለን፤ ኢትዮጵያንም እናስቀጥላለን"ብለዋል፡፡

''ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መልሶ ግንባታ የሚያደርገው ሁለንተናዊ ተሳትፎና ጥረት የሚደነቅ ነው'' ያሉት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከ11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ በአሸባሪው ቡድን ውድመት ቢደርስበትም መንግስት ዳያስፖራውንና ሌላውንም በማስተባበር መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ ነው።

በተለይም ዳያስፖራው በወገናዊ ተቆርቋሪነት ላደረገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከሰሞኑ ብርጋዴል ጀኔራል ካሣዬ ጨመዳ በተገኙበት በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበርና በወሎ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ካናዳ የሚገኘው ግሎባል ኤይድ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም