መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ለተፈናቀሉ ዜጎች 16 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

183

ደብረ ብርሃን፣ ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር በአሸባሪው ሸኔ ምክንያት ከምዕራብ ሸዋና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ለተፈናቀሉ ዜጎች 16 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር  ድጋፉን ዛሬ ለደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር አስረክቧል።

ድጋፉ የተደረገላቸው ዜጎች በሰሜን ሸዋ ዞን በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ናቸው።

250 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 500 አልጋዎች እና አልሚ ምግብ ከተደረጉት ድጋፎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ በሸኔ አሸባሪ ቡድን ተፈናቅለው በከተማዋ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር 20 ሺህ ደርሷል ብለዋል።

ማህበሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ሌሎች አካላትም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ተወካይ አቶ ማሞ ታደሰ በበኩላቸው ማህበሩ ደጋፊ የሌላቸውን አረጋዊያንን ከመርዳት ጎን ለጎን በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የመርዳት ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የበጎ አድራጎት ማህበሩ ከሰባት ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ሕሙማንን አሰባስቦ በመደገፍ ላይ መሆኑን ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም