የኢትዮጵያ የአንድ ቻይና ፖሊሲ አቋም ዛሬ የተጀመረ አይደለም - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

226

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ስታራምድ የቆየችውን የአንድ ቻይና ፖሊሲ አቋሟን እንዳጸናች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚስኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን የሚያጠናክር ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ማድረጓንም ተናግረዋል።

አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚከሰቱ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች እንደሚያሳስቧት ገልጸው፤ ሰሞኑን በቻይና-ታይዋን ጉዳይ የተከሰተውን ውጥረትም በትኩረት እየተከታተለች መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአንድ ቻይና ፖሊሲ አቋም ዛሬ የተጀመረ አይደለም ያሉት አምባሳደር መለስ፤ ከቻይና ጋር በነበረን ግንኙነት ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስታት አፅንተው የያዙት አቋም ነው ብለዋል።

አሁንም ኢትዮጵያ ለአንድ ቻይና ፖሊሲ ፅኑ አቋም እንዳላት ጠቁመው፤ ፖሊሲውን ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸው የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረትም የሚያራምዱት አቋም መሆኑን አክለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረትና ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች ጋር መወያየታቸውንም የጠቀሱት አምባሳደር መለስ፤ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም ደግመው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

መልዕክተኞቹም የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እንደገለጹ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን የሚያጠናክር ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በተለያየ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የውጭ ሀገር ዜጎችን የመኖሪያ ፈቃድ ለመስጠትና ለኢሚግሬሽን አሰራር አመቺነት ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው ዙር ምዝገባ ትናንት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

በዚህም 66 ሺህ ያህል የውጭ ዜጎች ምዝገባ መከናወኑን ጠቁመው፤ ያልተመዘገቡ ዜጎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ እንደማይሆን ተናግረዋል።

አምባሳደር መለስ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለጎረቤቶቿ ቀዳሚ ሥፍራ እንደምትሰጥ በማንሳት ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሁንም አበክራ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ እየተሠራ ሲሆን ለሀገራቸው ልማት የሚያደርጉትን ድጋፍም እንዲያጠናክሩ የተጀመሩ ጥረቶች ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም