በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የህዝብ፣ስደተኛና ፍልሰት ጉዳዮች ቢሮ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ድጋፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

109

አፋር ፤ ሐምሌ 27 ቀን 2014(ኢዜአ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የህዝብ፣ስደተኛና ፍልሰት ጉዳዮች ቢሮ እ.አ.አ በ2022 በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።

የቢሮው ምክትል ረዳት ጸሃፊ ኤልዛቤት ካምቤል በአፋር ክልል በሚገኘው ሰርዶ መጠለያ ጣቢያ የሚገኘውን የኤርትራ ስደተኞች ጣቢያ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን የመስክ ምልከታና ውይይት አድርገዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ምክትል ረዳት ጸሃፊዋ እንዳሉት መጠለያ ጣቢያውን ለስደተኞች ምቹ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

May be an image of 13 people, people sitting and people standing

በተለይም በመጠለያ ጣቢያዉ ለሚገኙ ስደተኞች አስፈላጊዉ የሰብአዊ ድጋፍ፣የምግብና ተያያዥ የሆኑ አቅርቦቶች በበለጠ ትኩረት እንዲደርሱ ከባለድርሻ አካላት ጋር አስፈላጊ የሆኑ ስራዎች እንደሚሰሩ የገለጹት ምክትል ረዳት ጸሃፊዋ እ.አ.አ በ2022 በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

በቀጣይም ተቋማቸዉ መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ በመቀጠል ከፌደራልና የክልሉ መንግስት አመራሮች ጋር ተቀራርበዉ እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና ስደተኞችን ለማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ምክትል ረዳት ጸሃፊዋ ተናግረዋል።

ለዚህም እንዲረዳቸዉ ከሠመራ-ሎግያ ከተማ ከንቲባ ጋር ጠቃሚ ዉይይት ማካሄዳቸዉን ገልጸዋል።

የሠመራ-ሎግያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱ ሙሳ በበኩላቸዉ ክልሉ የኤርትራ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተለይም የሰርዶ የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለሰመራ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከከተማዉ ነዋሪዎች ጋር በልማት የማስተሳሰር ስራዎች አንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።

በአፋር ክልል አይሳኢታና ሰርዶ መጠለያ ጣቢያ ከ61ሺ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ ከስደተኞች አገልግሎት ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም