የኢትዮጵያውያን የምክክር ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ የንግዱ ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

120

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያውያን የምክክር ሂደት ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በስኬት እንዲጠናቀቅ የንግዱ ማህበረሰብ የገንዘብና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርግ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት አምስት ወራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ ለምክክር የሚጠቅሙ ግብዓቶችን እየሰበሰበ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያውያን አጀንዳ በመሆኑ የጋራ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንድ አገር ውስጥ ሰላም ከሌለ የኢኮኖሚም ይሁን ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚስተጓጎል በመሆኑ በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ ዋነኛ ተጎጂ ይሆናል ነው ያሉት።

ሀገራዊ ምክክሩ ሰፊና የንግዱን ማህብረሰብ ጨምሮ ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ የሚከናወን አገራዊ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ሁለንተናዊ እገዛ የሚጠይቅ በመሆኑ በተለይም የንግዱን ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያውያን አጀንዳ በኢትዮጵያውያን ገንዘብና ጉልበት እንዲሁም እውቀት መመራት ስላለበት ኮሚሽኑ የውጭ ተቋማትን የገንዘብ ርዳታ እንደማያማትርና በአዋጅም የተከለከለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም በገንዘብ እጥረት ምክንያት አጀንዳው በውጭ ኃይሎች እንዳይጠመዘዝ የንግዱ ማህበረሰብ የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ኮሚሽኑና የንግዱ ማህበረሰብ በሀገራዊ ምክክሩ ውስጥ ሊካተቱለት የሚገቡ አጀንዳዎችን በተመለከተ በቀጣይ ውይይት እንደሚያደርግ የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን፤በአጀንዳዎቹ ላይ መግባባት ላይ እንደሚደረስም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና በዙሪያዋ ያለው ቀጣና ሰላም የደፈረሰበት አካባቢ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ምክክርና ውይይት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ለቀጣናው ተምሳሌት እንደሚሆን ጠቁመው የንግዱ ማህበረሰብ በአካባቢው ሀገራት ያለውን ትስስር ተጠቅሞ የምክክርን አስፈላጊነት እንዲያጎላ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም