በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚሰሩ ስራዎችን የክልሉ መንግስት በተገቢው መንገድ እንደሚደግፍ አስታወቀ

102

ወልዲያ፣ ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚሰሩ ስራዎችን የክልሉ መንግስት በተገቢው መንገድ እንደሚደግፍ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።

"ትምህርት አገርን የምንገነባበት፣ ዕውቀትና ባህልን ለቀጣይ ትውልድ የምናስተላልፍበት ዋና መሳሪያ በመሆኑ ለጥራቱ መጠበቅ ተጋግዝን መስራት ይገባናል'' ብለዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በወልዲያ ከተማ ባዘጋጀው የ2014 የትምህርት ዘመን የማጠቃለያ እቅድ ግምገማ እና የ2015 ዓ.ም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ምክክር መድረክ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት ያወደማቸውን የትምህርትና ሌሎች ተቋማትን መልሶ ስራ ለማስጀመር በተደረገ ርብርብ የተሻለ ውጤት መጥቷል።

በትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ በወረራ ማግስት ትምህርት ለማስጀመር ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ መቆየቱን ገልፀው፤ የትምህርት ተቋማት ቀደም ሲል ከነበሩበት በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት የፈንድ ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተቋማትን ደረጃ ማሻሻልና ሌሎች አጋዥ ተግባራትን በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረው፤ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ በበኩላቸው የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆን፣ መምህራን በስራ ገበታ በሰዓቱ አለመገኘት፣ የትምህርት ስራውን በቅድመ ሁኔታ መወጠርና ተዛማጅ ችግሮች ለዘርፉ እንቅፋት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ችግሮቹን ለማስወገድ ተጠያቂነትን በማስፈን ለመማር ማስተማሩ ስራ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

መጪው የትምህርት ዘመን ምዝገባ ጳጉሜ 04 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድ ገልጸው፤ መስከረም 09 ቀን 2015 ዓ.ም ትምህርት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

የትምህርት ጥራት መጓደል ችግሮችን ለመፍታት ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

''ቀደምት አባቶቻችን የተጠበቡባቸው የእጅ ስራዎች ለዛሬው ትውልድ መኩሪያ ናቸው'' ያሉት ደግሞ የአማራ ምሁራን መማክርት ምክር ቤት ኃላፊ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ናቸው።

“የማስተማር ዘዴዎቻችን በክህሎት ብቻ መሆን የለበትም፣ ሙዚቃው፣ ግብረ-ገብነቱ፣ ጽዳትና ውበቱ እስከ ላይኛው እርከን ድረስ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል።

የመምህራንን ክህሎት ማሻሻልና ሞራላቸውን የመጠበቅ ስራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ይህም ለመማር ማስተማሩ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦው እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም