ክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ለመስራት መዘጋጀቱን ገለጸ

61

ቦንጋ፣ ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ለመስራት መዘጋጀቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስታወቁ።

የሀገሪቱን እድገት ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ በእውቀት የተገነባ ዜጋ ማፍራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2014 ትምህርት ዘመን ማጠቃለያ ግምገማና የ2015 ትምህርት ዘመን የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ሲጀመር ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ያለ በቂ እውቀት የሚመራ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባር ዘላቂና አስተማማኝ ሊሆን አይችልም።

በመሆኑም የትምህርት ዘርፍን ማዘመንና ቅድሚያ ሰጥቶ በመደጋገፍ ከጥራት ጋር ለተያያዙ ችግሮችም መፍትሔ እየሰጡ መሄድን ይጠይቃል ብለዋል።

በእውቀት የተገነባ ዜጋ በመፍጠር ብልጽግናን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በክልሉ የሚገኙ ህጻናት የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ምቹና የመማሪያ ግብዓት የተሟላላቸው እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለዚህም መሳካት ቁርጠኛ አመራር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በየደረጃው ያለው አመራር ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የትምህርት ዘርፍ መፍትሄ የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በክልሉ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ለመተግበር  በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የትምህርት ጥራት ማነቆዎችን በተባበረ ክንድ መፍታት ያስፈልጋል በማለት ገልጸው፤ ለ2015 የትምህርት ዘመን ተገቢው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም