በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያና ፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ

191

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)በኮሎምቢያ ካሊ እየተካሄደ ባለው 19ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያና ፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

በሻምፒዮናው የሶስተኛ ቀን ውሎ ከቀኑ 11 ሰአት 3 ሺህ ሜትር ወንዶች ማጣሪያ አትሌት መልኬነህ አዘዘ እና አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ይሳተፋሉ።

አትሌት መልኬነህ 7 ደቂቃ ከ42 ሴኮንድ ከ95 ማይክሮ ሴኮንድ እንዲሁም አትሌት አብዲሳ 7 ደቂቃ ከ38 ሴኮንድ ከ79 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአት አላቸው።

በሁለት ምድብ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከየምድቡ ከአንድ እስከ ስድስት የወጡ እና የተሻለ ፈጣን ሰአት ያላቸው ሶስት አትሌቶች ለፍጻሜው ያልፋሉ።

ከቀኑ 11 ሰአት ከ35 በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች ማጣሪያ አትሌት ሳሙኤል ፍሬው እና አትሌት ሳሙኤል ዱጉና ይሳተፋሉ።

አትሌት ሳሙኤል ፍሬው 8 ደቂቃ ከ19 ሴኮንድ ከ82 ሴኮንድ እንዲሁም ሳሙኤል ጉዱና 8 ደቂቃ ከ27 ሴኮንድ ከ40 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአት አላቸው።

በሶስት ምድብ በሚካሄደው ማጣሪያ ከየምድባቸው ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ እና ስድስት የተሻለ ፈጣን ሰአት ያላቸው አትሌቶች ለፍጻሜው ያልፋሉ።

ከሌሊቱ 7 ሰአት ከ55 ሰአት የ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ኤርሚያስ ግርማ እና አትሌት አድሃና ካሳዬ ይወዳደራሉ።

ከሌሊቱ 8 ሰአት ከ10 ደቂቃ በ800 ሜትር አትሌት ቅሳነት አለም ይሳተፋሉ።አትሌት ቅሳነት ትናንት በግማሽ ፍጻሜ ውድድር ከምድቧ ሁለተኛ በመውጣት ለዛሬው የፍጻሜ ውድድር ማለፏ ይታወሳል።

በ800 ሜትር ሴቶች ግማሽ ፍጻሜ የተወዳደረችው አትሌት ወዛም አረፋዮ ከምድቧ አምስተኛ በመውጣት ለፍጻሜው አላለፈችም።

ኢትዮጵያ በ19ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እስካሁን አንድ ወርቅ እና አንድ ብር በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

አሜሪካ በሁለት ወርቅ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን እየመራች ነው።ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ በተመሳሳይ አንድ ወርቅ እና አንድ ነሐስ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሻምፒዮናው እስካሁን 19 አገራት ሜዳሊያ አግኝተዋል።የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም