የውጭ ጫናዎችን በመመከት ሂደት የዳያስፖራው ተሳትፎ የላቀ ውጤት እንደተመዘገበበት ተገለጸ

131

ሐምሌ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ ይደረጉ የነበሩ የውጭ ጫናዎችን በመመከት ሂደት የዳያስፖራው ተሳትፎ የላቀ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እድሪስ፤ በ2014 በጀት ዓመት አጠቃላይ የዳያስፖራውን ተሳትፎና የተገኙ ውጤቶችን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ የውጭ ጫና የበረታበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰው፤ ይደርስ የነበረውን ጫና ለመመከትና እውነታውን ለማሳወቅ የዳያስፖራው ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ተናግረዋል።

በአንድ ቀን በ40 የተለያዩ የዓለም አገራት ሰልፍ በማድረግ የኢትዮጵያን እውነታ ያስተጋቡበት ታሪካዊ አጋጣሚም በዲፕሎማሲው መስክ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው ስለመሆኑም አንስተዋል።

የዳያስፖራውና ሌሎችም አካላት ጥረት በኢትዮጵያ ላይ ይደረጉ የነበሩ ያልተገቡ ጫናዎች እየረገቡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የዲፕሎማሲ ጫና በአንጻራዊነት እየቀነሰ በመሆኑ የታገዱ የብድርና ሌሎች ስምምነቶችም መተግበር መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በ2014 በጀት ዓመት የዳያስፖራው ተሳትፎ ከዲፕሎማሲው ባለፈ በኢትዮጵያ ልማትና ኢንቨስትመንት ላይ የላቀ እንደነበር ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ለሚሹ 1 ሺህ 800 ዳያስፖራዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ በዚህም ከ156 በላይ ዳያስፖራዎች ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸውን የመሬትና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

የዳያስፖራው ተሳትፎ “እኔም ለሀገሬ፣ ሀገሬም ለእኔ” በሚል መሪ ሃሳብ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ከዳያስፖራው 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ለቤተሰቦቻቸው ወይም ወደ ሀገር ቤት ከሚልኩት የውጭ አገር ገንዘብ (ሪሚታንስ) መግኘቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም