የክልሉን ችግሮች በመፍታት ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

141

ወልዲያ፤ ሐምሌ 25/2014 (ኢዜ )፡ የክልሉን ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

በሰሜን ወሎ ዞን በ2014 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የወረዳ፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የዞን መስሪያ ቤቶች እና ግለሰቦች የእውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር ዛሬ በወልድያ ከተማ ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የሰሜን ወሎ ዞን የአሸባሪው ህወሓት ወረራ ሰለባ በመሆኑ በርካታ ችግሮችንና ፈተናዎችን አስተናግዷል።

የዞኑ ህዝብ  በወረራ ውስጥም ሆኖ ለመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መረጃ በመስጠት፣ ስንቅና ትጥቅ በማቀበልና በግንባር ተሰልፎ ባደረገው ትግል አሸባሪው ቡድን አከርካሪውን ተመቶ እንዲመለስ መደረጉን አስታውሰዋል።

''አሸባሪው ህወሓት በክልላችን ህዝብ ላይ ያደረሰው የህይወት መጥፋት፣ የሀብት ውድመትና ዘረፋ አልበቃው ብሎ አሁንም የጦርነት ጉሰማውንና ትንኮሳውን አላቆመም'' ብለዋል።

ህልውናችን የሚረጋገጠው የውስጥ አንድነታችን አጠናክረን ንቁና ዝግጁ ስንሆን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ የክልሉን  ችግሮች በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በፍጥነት በመፈጸም፣ የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ፣ ሠላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ህዝቡ መንግስትን የመደገፍ ሚናውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋምና ለመገንባት የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ለመተግበር የሚያስችል ጽህፈት ቤት በማቋቋምና የሰው ሃይል ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን  አስገንዝበዋል።

የአማራ  ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ መላው ህዝብ በየሙያ ዘርፉ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

አመራሩ፣ ባለሙያውና ህዝቡ አንድ በመሆን የተጀመረውን ለውጥ ዳር ለማድረስ መትጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።

 አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ደግሞ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋው ባታብል ናቸው።

''ህዝቡ ከጥምር ኃይሉ ጎን በመሰለፍ ወራሪውን ኃይል መመከት በመቻሉ ላገኘነው ድል በቅተናል'' ብለዋል።  

በመርሐ ግብሩ በ2014 የበጀት አመት በስራቸው ብልጫ ላሳዩ የወረዳና ከተማ አስተዳዳሮችና ግለሰቦች የዋንጫና ምስክር ወረቀት ከክብር እንግዳው እጅ ተቀብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም