የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች በበላይነት የሚመሩትና በኢጋድ ቀጣና ሰላምና ልማት ላይ የሚንቀሳቀስ ፎረም በይፋ ሥራ ጀመረ

101

ሀምሌ 25/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች በበላይነት የሚመሩትና በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጣና ሰላምና ልማት ላይ የሚንቀሳቀስ ፎረም በይፋ ሥራ ጀመረ።

የአንተርፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ደርጅት በይፋ ሥራ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዲስአበባ እየተካሄደ ነው።

በመርኃ ግብሩ ላይ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የፎረሙ የቦርድ ሰብሳቢ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣  የፌደራልና የክልል መንግሥታት አመራሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች ተወካዮች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

ፎረሙ በንግዱ ማህበረሰብ አነሳሽነት መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም መቋቋሙ የተገለጸ ሲሆን ባለፉት ወራትም ህጋዊ ሰውነት የማግኘትና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቶ ዛሬ በይፋ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱን አብስሯል።

የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የፎረሙ የቦርድ ሰብሳቢ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ፎረሙን በበላይነት የሚመሩ ሲሆን የሀገሪቱ ታዋቂ ባለሃብቶች በመስራችነትና በአባልነት ተሳትፈውበታል።

ፎረሙ በኢትዮጵያና በኢጋድ ሀገራት በስፋት የሚስተዋሉ የሰላም እጦትና የደህንነት ስጋቶች እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው የንግዱ ማህበረሰብ በግንባር ቀደምትነት እንዲሰለፍ ለማድረግ መቋቋሙም ተጠቁሟል።

ፎረሙ የንግዱ ማህበረሰብ በሰላም ጠበቃነት ዙሪያ በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጣና በተናጠልና በጋራ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖረውና በቀጣናው የልማት ጉዳዮች የንግዱን ማህበረሰብ ትስስርና ተደማጭነት ለማጎልበት እንደሚሰራ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም