ሻደይ የልጃገረዶች በዓል አንድነትና መተባበርን በሚያንፀባርቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

163

ሰቆጣ (ኢዜአ) ሐምሌ 24/2014 በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሻደይ የልጃገረዶች በዓል ኢትዮጵያዊ አንድነትና መተባበርን በሚያንፀባርቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የዘንድሮው የሻደይ በዓል "ሻደይ ኢትዮጵያ በግንባር፣ ለድል፣ ለአንድነትና ለክብር" በሚል መሪ ቃል ከነሀሴ 16 እስክ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እንደሚከበር ታውቋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስቡህ ገበያው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ የሻደይ በዓል ከጥንት ጀምሮ ህብረተሰቡ ባህሉን የሚያንጸባርቅበት ነው።

"የበዓሉ ተሳታፊ ሴቶችም በዘር፣ በቀለምና በሌላም ሳይለያዩ ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር በመሆን ባህላቸውን፣ ሃሳባቸውንና ምኞታቸውን በአደባባይ የሚገልጹበት በመሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል" ብለዋል።

በዓሉ የአንድነት፣ የመፈቃቀርና የመከባበር ተምሳሌት በመሆን ለዘመናት ዘልቆ መቆየቱን ገልጸው፣ በአሁኑ ትውልድም በጉጉት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአሸባሪው ህወሓት ወረራና በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት የሻደይ በዓል በአደባባይ ሳይከበር አልፋል።

"ይህም መጥፎ አሻራ ጥሎ ማለፉን አልፏል" ብለዋል።
የኢትዮጵያዊነት ማንነት መገጫ የሆነውን የሻደይ በዓል በሃገር አቀፍ ደረጃ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት እንደሚከበርም ገልጸዋል።

"በዓሉ በሲምፓዚየም፣ በልጃ ገረዶች ባህላዊ ጨዋታና በተለያዩ ዝግጅቶች ስለሚከበር የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚችን ለመሳብ ያግዛል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የመፍረስ አደጋ የተጋረጠበት የውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የማስጎብኘትና ከተጋረጠበት እደጋ እንዴት መከላከል ይቻላል በሚለው ላይ የውይይት መድረከ እንደሚካሄድ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።  

የዘንድሮው የሻደይ በዓል ከአንድነትና ከፍቅር ባለፈ አልደፈር ባይነትን በሚያፀባርቅ መልኩ እንደሚከበርም አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ መከታና ነጸብራቅ ከሆነው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን የሻደይን በዓል ለሃገር አንድነትና ክብርን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንደሚከበርም ጠቁመዋል።
የሻደይ በዓል የመላ ኢትዮጵያዊያን በዓል በመሆኑ በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሰቆጣ ከተማ ተገኝተው በዓሉን እንዲታደሙም ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም