በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያመጣነው ውጤት በትብብር ከሰራን ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ አሸናፊ ማድረግ እንደምንችል ያመላከተ ነው

199

ሐምሌ 21/2014 (ኢዜአ) በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያመጣነው ድል በትብብር ከሰራን ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ አሸናፊ ማድረግ እንደምንችል ያመላከተ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሻምፒዮናው ድል ያስመዘገቡ አትሌቶች ተናገሩ፡፡

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በአሥር ሜዳሊያዎች ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በድል ለተመለሰው የአትሌቲክስ ቡድንም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የአቀባበልና የምስጋና መርሃ-ግብር ተከናውኗል፡፡

በውድድሩ ለተካፈሉ አትሌቶችና አሰልጣኞችም እንዳስመዘገቡት ወጤት መጠን ከ50 ሺህ ብር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው አትሌቶች፤ በውድድሩ የተሳተፉ አትሌቶች በትብብር በመስራት ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳልያ ያገኘችው አትሌት የወርቅውሃ ጌታቸው፤ አትሌቶች ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ በትብብርና መተጋገዝ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ነው ያነሳችው፡፡

አንድነት ኃይልና የአሸናፊነት ምስጢር መሆኑን ገልጻ፤ ከዚህ አኳያ ልክ እንደ አትሌቲክሱ በሁሉም መስክ በመተባበር ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጻለች፡፡

በውድድሩ በማራቶን ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ያገኘው አትሌት ታምራት ቶላ በበኩሉ፤ ከተባበርን ታላላቅ ድሎችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ያገኘነው ድል አመላካች ነው ብሏል።

"አንድነት የድል ተምሳሌት ነው፤ አንድ ስንሆን ሁሌም አሸናፊ ነን" በማለትም መልእክቱን አስተላልፏል።

በዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ጠንካራ ትብብር ማድረጋቸውን የገለጸችው ደግሞ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል የነሃስ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት መቅደስ አበበ ናት፡፡

መተባበርና መተጋገዝ የኢትዮጵያዊያን እሴት መሆኑን የተናገረችው አትሌት መቅደስ፤ በቀጣይም ትብብራችንን በማጠናከር ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ አለብን ነው ያለችው፡፡

በማራቶን ውድድር የብር ሜዳልያ ያገኘው አትሌት ሞስነት ገረመው፤ "ወደ ውድድሩ ያቀናነው ለግል ሜዳልያ ለማስመዝገብ ሳይሆን ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ ነው፤ በዚህም ተሳክቶልናል" ብሏል፡፡

በቀጣይም መሰል ትብብሮችን በማጠናከር ኢትዮጵያን ለተጨማሪ ድሎች ለማብቃት መዘጋጀት አለብን በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም