የኢትዮጵያ የአሸነፊነት ሚስጥር ልጆቿ በአንድነትና በትብብር የመስራት ውጤት ነው- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

135

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 21/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአሸነፊነት ሚስጥር ልጆቿ በአንድነትና በትብብር የመስራት ውጤት እንደሆነ የጀግኖች አትሌቶቻችን አኩሪ ድል ማሳያ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።
‘‘አንድ ሆነን እንስራ ኢትዮጵያ ታሸንፍ’’ በሚል መሪ ሀሳብ  በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች የምስጋና መረሃ ግብር ዛሬ በክልሉ የተለያዩ  ተቋማት ተካሄዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያዊያን  በአንድነትና በትብብር ከሰሩ በድል አድራጊነት የማይሻገሩት ፈተና አይኖርም።

ለዚህም ሰሞኑን በአሜሪካ  በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን የሀገርን ክብር በማስቀደም በአንድነትና በትብብር በመስራት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያበሰሩ  አትሌቶች ዋነኛ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በአንድነትና በትብብር መስራትን በማጠናከር የኢትዮጵያን የአሸናፊነት አስጠብቆ  የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ  ለማሳካት  በርትቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይም  ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ሁሉም በህብረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳሰበዋል።

በ18ኛ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  የኢትዮጵያን ስምና ዝና ከፍ ላደረጉ ጀግኖች አትሌቶች የክልሉ ህዝብና መንግስት ከፍተኛ ምስጋና የሚቸራቸው ነው ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ትሁት ሐዋሪያት በበኩላቸው፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን  በአንድነት ከተጓዝን የማንሻገረው ፈተና አይኖርም ብለዋል።

በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስምና ሰንደቅ ዓላማ   ከፍ ላደረጉ አትሌቶች ድል ለዘላለም ሲወደስ የሚኖር ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ስፖርት  ኮሚሽነር አቶ ታይዶር ቻምባንግ ናቸው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም