ለትምህርት ስርዓቱ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው...የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

76
ባህርዳር መስከረም 5/2011 በትምህርት ስርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ውጤታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። በአማራ ክልል 12ኛ ክፍል ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 102 ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማትና የእውቅና ስነ-ስርዓት ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተካሒዷል። የቢሮ ሃላፊው ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ስርዓቱ ዋና ዓላማ ወጣቱን ትውልድ ወቅቱ በሚጠይቀው እውቀትና ክህሎት መገንባት ነው። ከሀገራችን የትምህርት ስርዓት መለኪያ አንዱ በሆነው የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ላይ ክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ባመጡ በሚለው መለኪያ አንደኛ እየወጣ መምጣቱ የሚበረታታ ነው። "ለዚህም የመምህራንና የትምህርት አመራሩ፣ ቤተሰብ፣ ተማሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ ካላት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል። በ2010 በጀት ዓ.ም ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡት የተደረገው ሽልማት በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በርትተው በመስራት የሀገር እድገትን የሚያስቀጥል እውቀት፣ ክህሎትና ስነ-ልቦና ሰንቀው እንዲወጡ የሚያስችል ነው። "በተጨማሪም ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በክልል በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ላይ መነሳሳትና የተሻለ ውድድር ለመፍጠር ያለመ ነው'' ብለዋል። የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባኤ አቃቤ ነዋይ የሆኑት ፕሮፌሰር ኢንጅነር ዳንኤል ቅጣው “አባቶቻችን የነጻነትና የሉዓላዊነት አሻራ እንዳወረሱን ሁሉ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰውን አስበን መስራት አለብን” ብለዋል። ወደ ዩንቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች አብሮነትን መላበስ፣ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም፣ በመማከር ውጤታማ መሆንና የንባብ ባህልን ማጎልበት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ውጤት 640 በማስመዝገብ በክልሉ አንደኛ የወጣው ተማሪ ሃይለ ሚካኤል ሞላ እንዳለው ላገኘው ውጤት የቤተሰቦቹ፣ የመምህራንና የጓደኞቹ እገዛና ድጋፍ ወሳኝ ነበር። በተለይም ተማሪዎች የራሳቸውን የጥናት ልምድ ከሌሎች ተሞክሮ በመውሰድ በውጤታማነት በመመዘን ማስቀጠል እንዳለባቸው ምክሩን ለግሷል። 619 ውጤት በማምጣት ተሸላሚ የሆነችው በእምነት አሸናፊ በበኩሏ ጠንክራ በማጥናቷ አሁን ላገኘችው ውጤት መብቃቷን ተናግራለች። 600 እና ከዛ በላይ ውጤት ያመጡ 12 ተማሪዎች ላፕቶፕ፣ 6ሺህ ብር፣ ሻንጣ፣ አንሶላና ብርድ ልብስ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ሌሎቹም እንደየውጤታቸው 5ሺህ እና አራት ሺህ ብር እንዲሁም ሻንጣ፣ አንሶላና ብርድ ልብስ ተሸልመዋል። የክልሉ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ 12 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ላፕቶፕ በመሸለማቸው ምስጋና ተበርክቶላቸዋል። ጥረት ኮርፖሬት በበኩሉ ለ102ቱ ተማሪዎች የሻንጣ፣ የአንሶላና ብርድ ልብስ ሽልማት ሲያበረክት የክልሉ መንግስት የገንዘብ ሽልማት አድርጓል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም