የጋላፊ-ኤሊደአር-በልሆ አስፓልት መንገድ ግንባታ ከግማሽ በላይ ተጠናቀቀ

145
ሰመራ መስከረም 5/2011 የጋላፊ ኤሊደአር በልሆ ድረስ 78 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ  ከግማሽ በላይ መጠናቀቁን  የፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ገለጹ፡፡ የመንገዱ ግንባታ የሚካሄደው በተመደበለት ከሁለት ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ የፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ኢጅነር ግርማ አበበ እንደገለጹት የመንገዱ ግንባታ በተያዘው ዓመት እንዲጠናቀቅ ታቅዶ ጥቅምት 2008 ዓ.ም. በመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት ተቋራጭነት የተጀመረ ነው፡፡ መንገዱ ከሚሸፍነው 78 ኪሎ ሜትር ውስጥ የ67 ኪሎ ሜትር የመሬት ሙሌት የተጠናቀቀ ሲሆን ከዚህም 32 ኪሎ ሜትሩ በኮንክሪት አስፓልት ለብሷል፡፡ የቀረው የ11 ኪሎ ሜትር የመሬት ሙሌትና ተጓዳኝ ስራዎች ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከተቋራጩ  ጋር መግባት ላይ መደረሱን የፕሮጀክቱ ተቆጣጠሪ መሐንዲስ ተናግረዋል፡፡ ከአጠቃላይ የመንገዱ ውስጥ እሰካሁን 55 በመቶ መከናወኑን ጠቅሰው በውሉ መሰረት መጠነኛ መዘግየት እንደታየበት  አመልክተዋል፡፡ የዘገየበትም ምክንያት የኮንክሪት አስፓልት በባህሪው የሚያስፈለገውን ከፍተኛ ውሃ  እጥረት በማጋጠሙ ቢሆንም ችግሩን በመፍታት ግንባታው ለማፋጠን ጥረት እየተደረገ መሆኑን መሐንዲሱ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ በበኩላቸው እየተገነባ ያለው መንገዱ የሃገሪቱ ገቢና ወጪ እቃዎች ለማስተናገድ በዋናው የጂቡቱ ወደብ የሚታየውን መጨናነቅ እንደሚያስቀር ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሰት የታጁራ ወደብን አንዱ አማራጭ አድርጎ ለመጠቀም የጀመረው ስራ አካል ነው፡፡ መንገዱ ከጋላፊን አስከ ጅቡቲ ድንበር በልሆ ድረስ እንደሚያገናኝና በተመሳሳይ በጅቡቲ መንግሰት በኩልም የመንገዱ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ሳምሶን ተናግረዋል፡፡ ይህም ዋነኛ ሀገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴን በማፋጠን በዘርፉ የሚያጋመውን አላስፈላጊ የጊዜና ወጪ ብክነት ለማስቀረት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ "በተጨሪም 64 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ርዝመት አሰብ መንገድ አካል በመሆኑ ሁለቱን ወደቦች ለመጠቀም እድል ይሰጣል" ብለዋል አቶ ሳምሶን፡፡ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በባለስልጣኑ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በኤሌደአር ከተማ በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ዋሲሁን  ደስታ በሰጡት አስተያየት የመንገዱ መገንባት  ከተማዋን  ከመሀል ሀገር ጋር ጭምር በቀላሉ በማገናኘት ለንግድ እንቅስቃሴው መቀላጠፍ  ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አቶ አህመድ ሙሳ መንገዱ ለአካባቢው አርብቶ አደር ማህበረስብ ልማትና  እድገት መፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም