የአማራ ክልል ምክር ቤት መንግስት እየተከተለ ያለውን የሰላም አማራጭ ይደግፋል -አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

183

ባህር ዳር፣ ሐምሌ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) "መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተከተለ ያለውን የሰላም አማራጭ የክልሉ ምክር ቤት ይደግፋል" ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ ማካሄድ ሲጀምር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አፈ ጉባኤዋ "አሸባሪው የህወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት በክልሉ ህዝብ ላይ በርካታ ሰብዓዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች ደርሰዋል" ሲሉ አስታውሰዋል።

የአማራ ክልል መንግስት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ለመደገፍ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

መንግስት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ አሁን እየተከተለ ያለውን የሰላም አማራጭ የአማራ ክልል ምክር ቤት እንደሚደግፍም ገልጸዋል።

ግጭት የሚፈታው በጦርነት ብቻ እንዳልሆነ የክልሉ ምክር ቤት እንደሚያምን አመልክተው፤ "የሰላም አማራጩ የኢትዮጵያን ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚያስከብር እንዲሆን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ነን" ብለዋል።

May be an image of 1 person and standing

የሰላም አማራጭ በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚሳካ እንዳልሆነ ገልጸው፤ አሁንም በድንበር አካባቢ ተጨባጭ ትንኮሳዎች እየታዩ በመሆኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት የህልውና ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅና ህግ ማስከበር ላይ በትኩረት ሲሰራ እንደነበር ያስታወሱት አፈ ጉባኤዋ፤ በተጠና መንገድ በተከናወነው ህግ የማስከበር ስራ ዜጎች ሰላም ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህብረተሰቡ ፍላጎት መሆኑን አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚያካሂደው ጉባኤ የሥራ አስፈጻሚ አካላት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የንጋት ኮርፖሬት የ2014 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶችን ገምግሞ ማጽደቅ እንዲሁም፤ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም