“የጊዜው ጉም ያልጋረደው ጽናት”

753

           በይሁኔ ይስማው

የተለያዩ አገራት ተወዳዳሪ ስፖርተኞቻቸውን መልካም ተመኝተው፣ ባንዲራ አልብሰውና የጀግና አሸኛኘት አድርገው ወደ ሥፍራው ከሸኙ ውለው አድረዋል።

በውድድር ተሳታፊ ለመሆን ስፖርተኞችን የላኩ አገራት በሚችሉት አጋጣሚ ሁሉ የወከሏቸውን አትሌቶች ውጤት ለማየት እየተጠባበቁ ሲሆን ተሳታፊ አትሌቶች ትጥቃቸውን አጥብቀውና መማቸውን ጠብቀው ለውድድሩ እያሟሟቁ ይገኛሉ።

በመሮጫ መሙ ላይ በአረንጓዴው ማሊያቸው ተውበው በፍጹም ልበ ሙሉነት የኢትዮጵያ ወኪሎች አትሌት ቦሰና ሙላት፣ እጅጋየሁ ታዬ እና ለተሰንበት ግደይ ተሰልፈዋል።

የውድድሩን መጀመር የሚያበስረው ሽጉጥ ሲተኮስ የረዥሙ ጉዞ ትንቅንቅ ተጀመረ።

አይበገሬዎቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች እርስ በርስ እየተናበቡ በአሸናፊነት አጠናቀው ሰንደቃቸውን ከፍ ለማድረግና የአገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ ከዓለም አትሌቶች ጋር ፍልሚያውን ተያያዙት።

በሚገርም ቅንጅትና የቡድን ሥራ በብዙ ዓመት አንዴ በሚከሰት አይነት ትንቅንቅ ሁሌም ከአዕምሮ  የትውስታ መዝገብ የማይፋቅ  ታሪካዊ የሆነ ድል አድራጊነት በሽርፍራፊ ሴኮንድ ልዩነት ለተሰንበት ግደይ በውድድሩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስመዘገበች።

ለተሰበት ግደይ ከኬንያዊቷ ሄለን ኦብሪና ማርጋሬት ችሊሞ ጋር የመጨረሻው ሴኮንድ ትንቅነቅ ተመልካቾችን ብድግ ቁጭ ያደረገ ነበር።

የውድድሩ ትዕይንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከ22  ዓመት በፊት ከኬንያዊው አትሌት ፖልቴርጋት ጋር ያደረገውን ትንቅንቅ ያስታወሰ ክስተት ነበር።

በዚህ ድል የውድድሩ አሸናፊ ለተሰንበት ግደይ ለፈጣሪዋ ምስጋናዋን እየቸረች ሰንደቁን ለብሳ ደስታዋን ስትገልጽ በቴሌቪዥንም ይሁን በአካል ተገኝተው ውድድሩን ይከታተሉ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን አብረው ጮቤ ረገጡ።

ለዚህ ድል መገኘት አትሌት እጅጋየሁ ታዬ የነበራት የላቀ ሚና በብዙ የስፖርት ቤተሰቦችና የውድድሩ ተንታኞች ተወድሷል።

የውድድሩ አሸናፊ አይበገሬዋ አትሌት ለተሰንበት የኢትዮጵያን የድል ብሥራት በማስጀመር በኦሪገን ለውድድር የተሰለፉትን ኢትዮጵያዊያን ለሌላ ድል በማዘጋጀት የአሸናፊነት የሞራል ስንቅ አቀብላለች ማለት ይቻላል።

በወንዶች ማራቶን ደግሞ አትሌት ታምራት ቶላ፤ የአገሩን ልጅ በማስከተል የኢትዮጵያን ድል እና ደስታ እጥፍ ድርብ አደረገው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና የቡድኑ መሪ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በሻምፒዮናው ከማበረታታት ባለፈ የኢትዮጵያ አትሌቶች ባሸነፉባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ በደስታ ሲቃ በእንባ ታጅባ ከአትሌቶቹ ጋር ደስታዋን ለመላ ኢትዮጵያዊያን አጋብታለች።

በተወዳዳሪነት ዘመኗ በአሸናፊነት የኢትዮጵያዊያን የሃሴት ምንጭ የነበረችው ደራርቱ በመሪነት ዘመኗ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የብርታትና ፅናት ተምሳሌት በመሆን ለኢትዮጵያዊያን የውድድሩ ድምቀት ሆናለች።

በ10 ሺህ ሜትር የሴቶች ውድድር፣ በማራቶንና በቀጣዩቹ ቀናት በተደረጉ ሌሎች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣  5 ሺህ ሜትር የሴቶችና ሌሎች ርቀቶች አንዱ ለአንዱ ብርታትና ሞራል በመሆን ተወዳዳሪዎቹ ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋል።

በዚህም ከሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት በአሜሪካ ኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአራት ወርቅ፣ አራት ብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በኦሪገን የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መሳተፍ ከጀመረችበት እ.ኤ.እ. ከ1983 የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጀምሮ ከተመዘገቡት ውጤቶች በሙሉ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው እ.ኤ.እ. በ2005 ፊንላንድ ሄልስንኪ የዓለም ሻምፒዮና ሦስት ወርቅ፣ አራት ብርና ሁለት ነሐስ ባገኘችበት አጋጣሚ ሲሆን ዘንድሮ የተገኘው ድል ከዚህም ከፍ ያለ ሆኗል።

በዚህም አሸናፊ የሆኑና ድል ያደረጉ ጀግና አትሌቶች ስምና ክብራቸው ሁሌም በታሪክ ተሰንዶ የሚዘልቅ እንዲሁም በትውልድ ቅብብሎሽ በጀግንነት የሚወሳ ይሆናል።

በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመዘገበ ድል ለኢትዮጵያዊያንና ለተቀረው ዓለም ጭምር ከስፖርትም በላይ መልእክቱ ትልቅ መሆኑ እርግጥ ነው ።

የድሉ ትርጉም ከአሸናፊነትም በላይ እምነትና ጽናትን እንዲሁም በመተባበር አሸናፊ መሆን እንደሚቻል በተግባር የታየበት ሁነኛ ማሳያ ሆኗል።

የኢትዮጵያን ታላቅነትና በድል ተሻጋሪነቷ እንዳትቀጥል ለማደብዘዝ የሚጥሩ አካላት ከንቱ ድካም የማይሳካ መሆኑንም የኦሪገን ድል ትምህርት ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ በውጭ ጫና እና በውስጥ ተላላኪዎች እየተፈተነች ቢሆንም በቁርጥ ቀን ልጆቿ ከአሸናፊነቷ የሚገታት ምንም ኃይል እንደሌለና ኢትዮጵያዊነት ሳይደበዝዝ የሚዘልቅ ዘላለማዊ ክብር ስለመሆኑ አመላክቷል።

ሀገር የተለያየ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም እንኳ አትሌቶቻችን ሁሉንም ተቋቁመው በአንድ ልብ ኢትዮጵያን አስቀድመው ድል ያደረጉበት ምስጢር ችግሮች ጊዜያዊ ጉም እንጂ ዘላቂ አለመሆናቸውን አይተንበታል።

ኢትዮጵያን በልባቸው ስለው በዓለም አደባባይ አግዘፈው ያሳዩንን ጀግኖች አትሌቶቻችን በህብረትና አንድነት ያመጡት ውጤት አንዱ በአንዱ ላይ ጣት ከመቀሳሰር ወጥተን በሁሉም መስክ ተባብረን ከሰራን የማንወጣው ዳገት እንደሌለ ሁነኛ ማሳያ ነው።