በዞኑ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ የቡና ችግኝ ተተክሏል-- ጽህፈት ቤቱ

210

ቀምቴ ሐምሌ 17/2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በተያዘው የክረምት ወራት 6 ሚሊየን የሚሆን የቡና ችግኝ መተከሉን የዞኑ የግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የቡናና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ ረታ ታደሰ እንዳሉት በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች  በመንግስትና በግል የቡና ችግኝ ጣቢያዎች ከተዘጋጀው 5 ሚሊዮን 915 ሺህ 937 የቡና ችግኝ አብዛኛው ተተክሏል፡፡

በዞኑ እስከ አሁን በቡና ችግኝ ከተሸፈነው 1ሺህ 770 ሄክታር በላይ መሬት መካከል ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የቡና ችግኝ በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን ገልጸዋል።

በኩታገጠም የለማው መሬት 499 ሄክታር መሬት መሆኑንም  ተናግረዋል ፡፡

የተተከሉ የቡና ችግኖች ከግብርና ምርምር ተቋማት የተገኙ፣ በሽታን መቋቋም የሚችሉና የተሻለ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በዞኑ በቡና ልማት ላይ ከተሳተፉት 38 ሺህ ከሚጠጉ አርሶ አደሮች መካከል 5ሺህ573 አርሶ አደሮች በቡና ኩታ ገጠም ልማት ላይ መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡

ከመደበኛ የእርሻ ስራቸው በተጓዳኝ በቡና ልማት ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ አርሶ አደሮች  ተናግረዋል፡፡

የአቤ ደንጎሮ ወረዳ የቦርቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዱላ ጌታ እንዳሉት ወረዳቸው ለቡና ልማት ተስማሚ በመሆኑ  እስከ  አሁን 5ሺህ  የቡና ችግኝ  መትከላቸውን ገልጸዋል።

4ሺህ የቡና ችግኞችን ለመትከል ባዘጋጁት መሬት ላይ ከሌሎች የሰብል ዘር ሥራቸው  ጎን ለጎን  እየተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ካለሙት የቡና ማሣ በዓመት እስከ 17 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙና በዘንድሮው ክረምት ለመትከል ካቀዱት 5ሺህ  ቡና ችግኞች መካከል 3ሺህ  መትከላቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ለሜሣ አብዲሣ ናቸው።

ቀሪውን 2ሺህ የቡና ችግኝ እስከ  ሐምሌ 30/2014  ድረስ ተክለው እንደሚያጠናቅቁ  ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም