ሽብርተኛው ሸኔን ለማጥፋት ከጸጥታ ሀይሉ ጎን በመሰለፍ እንሰራለን

83

ነገሌ ኢዜአ ሀምሌ 17.2014 ዓ.ም ሽብርተኛው ሸኔን ለማጥፋት ከጸጥታ ሀይሉ ጎን በመሰለፍ እንደሚሰሩ የጉጂ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ገለጸ፡፡
የጉጂ ዞን፣ የነገሌ ከተማና የሊበን ወረዳ የመንግስት ሰራተኞች በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ደርሚ አሊ ቡድኑ በኦሮሞ ህዝብ ስም በንጹሀን ላይ እያደረሰ ባለው የሽብር ጥቃት አዝነዋል፡፡
ሰራተኛውም የመንግስት ደጋፊ ተደርጎ ስለሚቆጠር በዛቻና ማስፈራሪያ የተጣለበትን ህዝባዊ ሀላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ ተከልክሎ የቁም እስረኛ ሆኗል ብለዋል፡፡
ቡድኑ በርካታ ንጹሀንን፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሴቶችን ገድሎ ንብረታቸውን አቃጥጥሏል የተረፈውንም ዘርፏል በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብም አፈናቅሏል ብለዋል፡፡
ጥቃቱ የሰው ህይወት ከማጥፋት አልፎ ሀገር አፍራሽ በመሆኑ ለቡድኑ ስንቅና ትጥቅ የሚያቀብሉትን ሲያጋልጡ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ፡፡
የሽብር ቡድኑን ደጋፊዎች በማጋለጥና ለጥምር የጸጥታ ሀይሉም በመረጃ በመስጠት የጀመሩትን ድጋፍና ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
የሊበን ወረዳ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ አቶ ኮንሶሌ ጠቼ የሽብር ቡድኑ በንጹሀን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ካላስቆምን ሁላችንንም ታሪክ ይጠይቀናል ብለዋል፡፡
ሽብርተኛው ሸኔ የህወሀት ጁንታ ቡድን ፈረስ ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ የእራሱ አላማ የሌለው እንደሆነ ውሎ አድሮም ቢሆን ገብቶናል ብለዋል፡፡
የውይይቱ ተካፋይ ወይዘሮ ፍልቅልቅ አሰፋ ተተኳሽ ጥይት ስኳርና መድሀኒት በሚያቀብሉ የቡድኑ ደጋፊዎች ሲያዙ በመንግስት አስተማሪ እርምጃ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነ ለሽብር ቡድኑ የሚላላኩና መረጃ የሚያቀብሉትን በማጋለጥ ንጹሀንን ከእልቂትና መፈናቀል ሀገርንም ከመፍረስ ለማዳን ሀላፊነት ወድቆብናል ብለዋል፡፡
ሀገር ለማፍረስ ከህዝብና ከመንግስት የተጣለባቸውን ሀላፊነት ትተው ከሽብር ቡድኑ ጋር የሚተባበሩ አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መክረዋል ጠይቀዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የደቡብ እዝ መከላከያ ሰራዊት የኋላ ደጀን አስተባባሪ አዛዥ ተወካይ ኮረኔል ግርማ አየለ ሽብርተኛው ሸኔ የመከላከያ ሰራዊቱን ምት መቋቋም ተስኖት ተበታትኗል ብለዋል፡፡
ቡድኑ ተበታተነ እንጂ ሙሉ በሙሉ ባለመጥፋቱ የቡድኑን የሽብር ጥቃቱ ለማስቆም ሰራተኛው ለጥምር የጸጥታ ሀይሉ የሚሰጠውን ድጋፍና ትብብር እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡
ሰራተኛውም ቢሆን በሙያውና በእውቀቱ ከህዝብና ከመንግስት የተጣለበትን ሀላፊነት በብቃት እንዲወጣ የሽብር ቡድኑን ተባባሪና ደጋፊዎች ማጋለጥ አለበት ብለዋል፡፡
የመንግስት ጥምር የጸጥታ ሀይሉ በሽብርተኛው ሸኔ ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ጥምር የጸጥታ ሀይሉን የሚመሩት የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም