ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የላከችው የቡና መጠን እ.አ.አ በ2021 የ196 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ቻይና ገለጸች

844

ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የላከችው የቡና መጠን እ.አ.አ በ2021 ቀደም ካለው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ196 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዳይሬክተር ጀነራል ዉ ፔንግ ገለጹ።

ዳይሬክተር ጀነራሉ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው የቡና ምርት ዋና መዳረሻዎች መካከል አንዷ ቻይና ናት ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

ቻይና እ.አ.አ 2021 ከኢትዮጵያ ያስገባችው የቡና መጠን እ.አ.አ በ2020 ከነበረው ጋር ሲነጻጻር 196 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱን አመልክተዋል።

“የኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ የምርት ዘመን በአራት እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል መስማቴ አስደስቶኛል” ብለዋል ዳይሬክተር ጀነራሉ።

May be an image of 1 person

የኢትዮጵያ ቡና በቻይናውያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት እንዳለውም ገልጸዋል።

ሳዑዲ አረቢያ፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ እንግሊዝና አውስትራሊያ የኢትዮጵያ የቡና ኤክስፖርት ዋንኛ መዳረሻ ከሆኑ አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት ወደ ተለያዩ አገራት ከላከችው 300 ሺህ ቶን ቡና 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር እንዳገኘች ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤