ዳያስፖራው አንድነቱን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

108

ሀምሌ 16/2014/ኢዜአ/ ዳያስፖራው አንድነቱን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንዳአ ጥሪ አቀረቡ፡፡

አቶ ታዬ ይህን ያሉት የሰላም ሚኒስቴር  ከኢትዮጵያ  ዳያስፖራ  አገልግሎት  ጋራ በመተባበር "ዳያስፖራው የሚኖርባቸው ሀገራት ተሞክሮዎች ለኢትዮጵያ የሃይማኖቶች መከባበር" በሚል መሪ ሀሳብ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ነው።

በውይይቱ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንዳአ  በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ላይ የተሞከሩ ጫናዎችን ለመቀልበስ በአንድነት በመቆም አይተኬ ሚና ተጫውተዋል።

ዳያስፖራዎች አሁንም ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገራቸው ሰላምና ልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት፣ በዘር እና በሌሎች ልዩነቶች ሳይከፋፈሉ ለሀገራቸው አንድነት እና ሁለንተናዊ ሰላም መስፈን ሊሠሩ ይገባል፡፡

"ልዩነቶቻችንንና ፍላጎቶቻችንን በማጥበብ ለሰላም መስፈን በቅንነት መተባበርና አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት አለብን" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ሃይማኖቶች ተከባብረው እና ተቻችለው የሚኖሩባት ታላቅ ሀገር መሆኗን ለዓለም ማሳየቷን አንስተዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በሃይማኖት ተከባብረው በመኖር አርዓያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ዜጎች በሃይማኖት ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባትን ኢትዮጵያዊ ባህል ማጎልበት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

ለዚህም የሌሎች ሀገራት መልካም ተሞክሮዎችን በመውሰድ ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት።

በውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችም የኢትዮጵያን የሃይማኖት መከባበርና መልካም ገፅታ ለዓለም በማስተዋወቅ በኩል ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ህብረተሰቡን በማስተማርና የሃይማኖት ተቋማትን ትብብር በማጠናከር በሃይማኖቶች መካከል ያለውን መከባበር ማጎልበት እንደሚገባ አብራርተዋል።

የመቻቻልና የመከባበር እሴት ከቤተሰብ ይጀምራል ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ በውይይቱ የተንሸራሸሩ የሀገራትን ተሞክሮዎች ቀምሮ ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም