የአፍሪካ ልማት ባንክ የ50 ሚሊዮን ዶላር የስጋት መጋራት ስምምነት አፀደቀ

525

ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ልማት ባንክ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማነቃቃት ከክሬዲት አግሪኮል ኮርፖሬት እና ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር የ50 ሚሊዮን ዶላር የአደጋ ስጋት መጋራት ስምምነትን አፀደቀ።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከክሬዲት አግሪኮል ኮርፖሬት እና ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር የ50 ሚሊዮን ዶላር የአደጋ ስጋት መጋራት ስምምነት አፅድቋል።

ስምምነቱ የአፍሪካ ባንኮች እና አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ደንበኞቻቸው በአህጉራዊ እና አለምአቀፍ ንግድ ላይ የበለጠ እንዲሳትፉ ያስችላቸዋል ተብሏል። በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ የ450 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ የንግድ ልውውጥ መጠንን ለመደገፍ ያለመ እንደሆነም ነው የተጠቆመው፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ የሰሜን አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ሞሃመድ ኤል አዚዚ እንደገለፁት ይህ ስምምነት በአህጉሪቱ አዲስ የንግድ እንቅስቃሴን ለማበረታታት በተለያዩ የአፍሪካ ተዋናዮች መካከል ያለውን እምነት ያጠናክራል፡፡

ይህም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዕውን መሆን ወሳኝና ተቋቋሚነትን ለመገንባት፣እድገትን ለመፍጠር እና ዕድሎችን እንዲሁም ስራዎችን የሚፈጥር ማገገምን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

የባንኩ የፋይናንሺያል ሴክተር ልማት ዳይሬክተር ስቴፋን ናሌታምቢ በበኩላቸው ይህ አጋርነት ለአፍሪካ ባለው ቁርጠኝነት የሚታወቀው ከክሬዲት አግሪኮል ኮርፖሬት እና ኢንቨስትመንት ባንክ የሀገር ውስጥ ባንኮችን የበለጠ በመደገፍ ተጨማሪ የንግድ ፋይናንስን ለመስራት ያስችላል በማለት ተናግረዋል።

ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምር፣ ሽርክናው ወደ 50 የሚጠጉ የሀገር ውስጥ ባንኮችን እና የንግድ ደንበኞቻቸውን በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መደገፍ እንደሚያሥችል ጠቁመዋል፡፡

በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ለዋና ዋና የንግድ ፍሰቶች እንደ ማነቃቂያ በመሆን ያገለግላል ተብሏል፡፡

የስጋት መጋራት ስምምነቱ በአፍሪካ ገበያዎች እያደገ የመጣውን የንግድ ፋይናንስ፣ ምግብ፣ ኢነርጂ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ጤና አጠባበቅ ባሉ አስፈላጊ የኢኮኖሚ ዘርፎች ፍላጎት ለማሟላት ያለመ ነው።

በተጨማሪም በበርካታ የአፍሪካ ኢኮኖሚዎች ውስጥ ምርታማ ብዝሃነትን ያበረታታል እንዲሁም የስራ እድል በመፍጠር የታክስ ገቢዎችን ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም