በክልሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገለጸ

81

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 16/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ የተገነቡ 697 የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የክልሉ የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የከተሞች ተቋማዊ የአቅም ግንባታና የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሻግሬ አቤልነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት በአለም ባንክ ፕሮግራም ተጠቃሚ በሆኑ 32 ከተሞች ነው።

ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶችም በበጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞላቸው ሲከናወኑ ከቆዩ 785 የልማት ፕሮጀክቶች መካከል መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከእነዚህ ውስጥም 697ቱ ፕሮጀክቶች በ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለህዝብ ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስረድተዋል።

ከቀሩት ፕሮጀክቶች ውስጥ 11ዱ አፈጻጸማቸው 80 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፤ 77ቱ ደግሞ የግንባታ ጊዜያቸው የሁለት ዓመት በመሆኑ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ የሚጠናቀቁ ይሆናል ብለዋል።

 124 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ  ድንጋይ ንጣፍና የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ 66 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የተፋሰስ ልማት፣የጎርፍ መከላከያና የድጋፍ ግንብ ስራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ከበቁት ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም 8 ነጥብ 7 ሄክታር የአረንጓዴ ልማት ስራዎች፣ 36 ድልድዮችና የከተሞችን ፅዳትና ውበት ለመጠበቅ የሚያግዙ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች መገንባታቸውን አብራርተዋል።

እንዲሁም የከተሞችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የትራፊክ መብራቶች ተከላን ጨምሮ 234 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር፣ የውስጥ ለውስጥ የመብራትና የውሃ መስመር ዝርጋታ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ከፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከተሞች መካከልም ነፋስ መውጫ፣ ባቲ፣ ከሚሴ፣ ወረታ፣ አዲስ ዘመንና ሌሎች ከተሞች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቻቸውን ቀድመው በማጠናቀቅ ማስመረቅ የቻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የልማት ስራዎቹ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ችግር ከማቃለል ባለፈ የአካባቢው ኢኮኖሚ እንዲነቃቃና ማህበራዊ ኑሮው እንዲሻሻል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

''ፕሮግራሙ 53 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል'' ያሉት አቶ አሻግሬ፤ በ2015 በጀት ዓመትም በፕሮግራሙ ዕድሉን ያላገኙ ሌሎች የክልሉን ከተሞች በማካተት ህዝቡን  የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ከ600 በላይ ከተሞች እንዳሉ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም