የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በፈጠራና ክህሎት የተሻሉ ወጣቶችን ማፍራት አለባቸው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

88

ሀምሌ 16/2014/ኢዜአ/ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በፈጠራና ክህሎት የተሻሉ ወጣቶችን ማፍራት አለባቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ከደረጃ 2 እስከ ደረጃ 5 በ124 የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስመርቋል።

May be an image of one or more people and people standing

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በሙያ፣ በክህሎትና በአስተሳሰብ የተሻሉ ባለሙያዎችን ለማፍራት ወሳኝ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማጠናከርና በመደገፍና ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ለማፍራትም አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በዚህም የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ማስቀጠልና መዳረሻ ግቦችን እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ሥልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ጸዳለ ተክሉ፤ በሙያና ክህሎት በማብቃትና የስራ ባህልን በማዳበር አገርን በጋራ ማሳደግ የሁሉም ድርሻ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በቴክኒክና ሙያ ሰልጥነው የተመረቁ  ወጣቶች አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በፈጠራ ታግዘው በመስራትና ለሌሎችም የስራ እድሎችን በመፍጠር ጭምር በተመረቁበት ሙያ ወደ ስራ ለመግባት መዘጋጀታቸውን ተመራቂዎች ተናግረዋል።

በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ከሚልን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም