በሴቶች ነገሥታትና መሪዎች ላይ ያተኮረው “ከማክዳ እስከ ሣህለወርቅ” የተሰኘው መጽሐፍ ተመረቀ

136

ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሴቶች ነገሥታትና መሪዎች ላይ ያተኮረው “ከማክዳ እስከ ሣህለወርቅ” የተሰኘው የደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ይልማ መጽሐፍ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በዛሬው ዕለት ተመርቋል ።

በምርቃቱ የተገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ ገብሬ፤ መጽሐፉ በሀገራችን የነበሩ ሴቶችን ሚና ለመረዳት ያገለግላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሴት መሪዎች በሰላሙ ጊዜ ሕዝብ እያስተባበሩ ሀገር ሲያለሙ፤ በጦርነት ጊዜ የባሎቻቸው ደጋፊዎችና  አማካሪዎች በመሆን  ለነፃነት ሲዋደቁ መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ደራሲው በሕይወት በነበሩበት ጊዜ  መጽሐፉን ያሰናዱበት ዋና ዓላማም የዛሬውና የነገው ትውልድ የሴት መሪዎችን ታሪክ አውቆ ለሀገሩ የበኩሉን ኃላፊነት በትጋት እንዲወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ዐቢይ ዓላማ ምክንያት በማድረግም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ ግንባር ቀደም መሪዎች ፣ የመሪዎች ደጋፊዎችና የልጆቻቸው ሞግዚቶች በመሆን ያገለገሉ ሴቶች ታሪክ በመጽሐፉ ተካቷል ብለዋል።

የመጽሐፉ ደራሲም በልዩ ልዩ የታሪክ ሰነዶችና የሃይማኖት መዝገቦች ውስጥ የነበሩ የታሪክ ውርሶችን አንድ ላይ ሰብስቦ በማጠናቀር ማቅረባቸው ለጥናትና ምርምር እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

የደራሲው ቅርብ ጓደኛና በመጽሐፉ ላይ የአርትኦት ሥራ የሠሩት አንጋፋው ደራሲ ገስጥ ተጫኔ በበኩላቸው መጽሐፉ በአመራር ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲም ከፍተኛ ሚና የተወጡ ሴቶችን ታሪክ ይዟል ብለዋል።

የነበራቸውንም የፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳይ ተሳትፎ ምን እንደነበር መጽሐፉ እንደሚያሳይም እንዲሁ።

መጽሐፉ በሴቶች እኩልነት ዙሪያ ለሚከናወኑ ተግባራት ካለፈው ዘመን የሴቶች ተሞክሮ ጋር እያነፃፀሩ ለመስራት የሀሳብ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ብዙ ሴቶች ወደ አመራር እየመጡ ቢሆንም በዘላቂነት የማኅበራዊ ተሳትፏቸውና የኢኮኖሚ እኩልነታቸው እንዲረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት መጽሐፉ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።

“ከማክዳ እስከ ሣህለወርቅ” የተሰኘው መጽሐፍ 34 ምዕራፎችና 340 ገፆች ያሉት ሲሆን ደራሲው መጽሐፉን ጽፈው ለማጠናቀቅ 10 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል።

ደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ይልማ ልብወለድና የታሪክ መጻሕፍትን በመድረስ የሚታወቁ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የበደል ካሣ ፣አገር የፈታ ሽፍታና የፖለቲካ አሽሙር የተሰኙ የልቦለድ መጻሕፍትን አሳትመዋል።  

“የሕይወቴ ሚስጥር” በሚል ግለታሪካቸውን ከማሳተማቸው በተጨማሪ የራስ አበበ ወልደ አረጋይ የሕይወት ታሪክ ላይ የሚያተኩረውን “የታሪክ ቅርስና ውርስ” እና “የልጅ ኢያሱ አነሳስና አወዳደቅ” የተሰኙ የታሪክ መጻሕፍትን ለአንባቢ አብቅተዋል።

‹‹ጋዜጠኝነት የወተት ጥርሴን የነቀልኩበት ሙያ ነው›› የሚሉት አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ አጥናፍ ሰገድ ይልማ፤ የሕይወት ሩጫቸውን ጨርሰው ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወቃል።