ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የቡናና የፍራፍሬ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ነው

153

ሆሳዕና፤ ሐምሌ 16/2014 (ኢዜአ) የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራ ጎን ለጎን በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የቡናና የፍራፍሬ ችግኝ ዝርያዎችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርስቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፀደቀ ላምቦሬ ለኢዜአ እንደገለጹትዩኒቨርስቲው በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በተለይ ዩኒቨርስቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር መሠረት በማድረግ ሰባት የምርምርማዕከላትን በመክፈት  ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ  እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በሰባቱም የምርምር ማዕከላት የአካባቢውን ስነ ምህዳር መሰረት ያደረጉ የቡና እና ኮረሪማ ዝርያዎችን ጨምሮ የመሬት መራቆትን የሚከላከሉ የደን እጽዋቶችን በማባዛት ለአካባቢው ማህበረሰብ  ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡአዲስ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት  ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

ዋናውን ግቢ ጨምሮ በምርምር ማዕከላቱ  በዋናነት የአቮካዶ፣ ቡናና አፕል ዝርያዎችን ለማስፋት የሚያስችል አመርቂ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከ700 ሺህ በላይ  የቡና፣ አፕልና ሌሎችንም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች እስከ ሚቀጥለው ዓመት ድረስ በማሰራጨት 250 ሺህ  የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል።

ዩኒቨርስቲው በሚያካሂደው የማህበረሰብ አገልግሎት ከተጠቃሚዎች መካከል በሾኔ ዙሪያ አጀባ ቦረራ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ወጣት አርሶ አደር   ዝናቡ  አየለ ከዩኒቨርስቲው  ምርምር ማዕከል በአነስተኛ ዋጋ 500የሚሆኑ  የቡና ችግኞችን በመግዛትና በመትከል እየተንከባከበ ነው።

የአካባቢውን ስነ ምህዳር መሰረት በማድረግ በዩኒቨርስቲው በምርምር ተሻሽለው የሚወጡ የቡና ቴክኖሎጂዎች በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ ስለሆነ አምራቹን ኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተናግሯል።

የቀድሞ የቡና ዝርያዎች  እስከ አምስት ዓመታት ጊዜ ቆይተው የሚሰጡትም ምርት አነሰተኛ ስለነበር አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዳልነበር አስታውሶ፤ ከዚህ ችግር የሚያላቅቁ ዝርያዎች በመገኘታቸው ልማቱን ለማስፋፋት እንደሚሰራ ገልጿል።

ባለፈው አመት ከምርምር ማዕከሉበመውሰድየተከሉት 100 የቡና ችግኝ በመጽደቁ በዘንድሮው ክረምትም ልማቱን ለማስፋፋት ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ በምስራቅ ባደዋቾ ወረዳ አንደኛ ጨፋ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ታረቀኝ ስምኦን ናቸው።

የቡና ምርት በገበያ ላይ ተፈላጊነቱ  እየጨመረ በመምጣቱ እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም  2 ሺህ የቡና ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን  ተናግረዋል።

ከዩኒቨርስቲው የወሰዱት የቡና ችግኝ የፅድቀት መጠን ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሩ፤ ይሄም በቀጣይ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አስረድተዋል።

በቡና ልማት ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በዩኒቨርስቲው እየተከናወነ ያለው የምርምር ስራ ውጤታማ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም