በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 49 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ጀምረዋል

103

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት 49 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት መነሻ ካፒታል ያስመዘገቡ ዘጠኝ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ በርካታ ውጫዊና ውስጣዊ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ያጋጠሟት ሲሆን ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችንም አስተናግዳለች።

ከእነዚህም መካከል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት፣ ድርቅ፣ የዜጎች መፈናቀል፣የአጎአ እድል ተጠቃሚነት መነሳት የኮቪድ ወረርሽኝ ተጠቃሽ ፈተናዎች ናቸው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሸን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሔኖክ አስራት፤ ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ ብታልፍም፤ በበጀት ዓመቱ አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መግባታቸውን ተናግረዋል።

አዳዲስ ባለሃብቶችን መሳብ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን እንዲሁም ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ረገድ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙዓለ ነዋይ ማፍሰስ የሚያስገኘውን ጥቅምና እድሎችን ለማስተዋወቅ ጠንካራ ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት።

በዚህም 49 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት መነሻ ካፒታል ያስመዘገቡ ዘጠኝ አዳዲስ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ባለሃብቶቹ በጨርቃጨርቅና በአቮካዶ ዘይት ማምረት ላይ መሰማራታቸውንም ነው ኃላፊው የጠቀሱት።

ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በትኩረት እየሠሩ መሆኑንም አቶ ሔኖክ ጠቁመዋል።

ለአብነትም ከውጭ ሲገባ የነበረውን የቢራ ብቅል በሀገር ውስጥ በማምረት ሙሉ በሙሉ መተካት መቻሉን ነው ያነሱት።

ኃላፊው አክለውም በ2015 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን ምቹ አማራጭ በማስተዋወቅ የተሻለ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማምጣት ዓላማ አድርጎ ከሰባት ዓመታት በፊት የተቋቋመ ነው።

እስካሁን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ከ120 በላይ ባለሃብቶች ገብተው እንዲሠሩ ማድረግ ተችሏል።

ከእነዚህ ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ግዙፍ የኢንቨስትመንት አቅም ያላቸው የውጭ አገር ባለሃብቶች መሆናቸውን አቶ ሔኖክ ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውሰጥ ከ83 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣት ሴቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም