በደቡብ ክልል 68 ተቋማት ከመመሪያ ውጪ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ግዢ ፈጽመዋል

114

ሐዋሳ፣ ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በ2014 በጀት ዓመት 68 ተቋማት ውስጥ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ግዢ ከመመሪያ ውጪ መፈጸሙን እንዳረጋገጠ የክልሉ ዋና ኦዲተር አስታወቀ።

ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ከመመሪያ ወጭ የውሎ አበል ክፍያ መፈጸሙ ማረጋገጡን ገልጿል።

የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ፈዲላ አደም ለምክር ቤቱ የበጀት አመቱን ሪፖርት አቅርበዋል።

መስሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ68 መስሪያ ቤቶች ባካሄደው የግዥ አፈጻጸም ኦዲት 87 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር በላይ ግዢ ከመመሪያ ወጭ እንደተፈጸመ ማረጋገጡን ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ኦዲተር መስሪያ ቤቱ በ100 መስሪያ ቤቶች ባካሄደው የክፍያ ኦዲት ከ22 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ከመመሪያ ውጪ የውሎ አበል ክፍያ መፈጸሙን እንዳረጋገጠ አመልክተዋል።

ስድስት ልዩ ኦዲቶችን ጨምሮ 237 ኦዲቶችን መካሄዱንም ዋና ኦዲተር ፈዲላ ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ገልጸዋል።

የጃጁራ ከተማ አስተዳርና ፋይናንስ ጽህፈት ቤት፣ የጌዲኦና የሃላባ ዞን ፋይናንስ መምሪያ፣ የሳውላና የሃላባ ማረሚያ ተቋም እንዲሁም የአረካ ከተማ ዙሪያ አርሶ አደሮች ሁለገብ ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ልዩ ኦዲት የተደረገባቸው ተቋማት ናቸው።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት በቀረበው የኦዲት ሪፖርትና በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ቋሚ እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት ሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው እለት ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም