የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወንድማማችነት መንፈስን ያጎለብታል - አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

77

ሐረር፤ ሐምሌ 15/2014(ኢዜአ) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎች ሃገራቸውን እንዲያውቁ ከማድረግ ባሻገር የወንድማማችነት መንፈስን የሚያጎለብት መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ አመለከቱ።

የቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ከሐረሪ ክልል ጋር በመሆን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀምረዋል፡፡

አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት በሀገሪቱ 131 ሺህ ችግኝ ለመትከል እየሰሩ ይገኛሉ።

May be an image of 3 people, people standing and outdoors

ከዚህ ውስጥም በሐረር ከተማ እና አካባቢው 20 ሺህ ችግኝ እንደሚተከል ጠቅሰው፤ የአቅመ ደካማ ዜጎች የመኖሪያ ቤት እድሳት እና የቅርስ ጥበቃ ስራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል ፡፡

የበጎ አድራጎት ስራን ባህል ሆኖ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ሚኒስትሯ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐግብር ዜጎች ሀገራቸውን እንዲያውቁ ከማድረግ ባሻገር የወንድማማችነት መንፈስን የሚያጎለብት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፤ የበጎ አድራጎት መረሐግብሩ ህብረተሰቡንና አመራሩን ያሳተፈ መሆኑን አመልክተው፤ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ተንከባክቦ እና ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የሁሉም ሀላፊነት መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተተከለው ችግኝ መጽቀዱን ጠቁመው፤ ዘንድሮ የተተከሉቱም በመንከባከብ ለፍሬ እንደሚያበቁ ተናግረዋል፡፡

በሐረር ከተማ አባዲር ወረዳ ቤታቸው ፈርሶባቸው የነበሩት የወይዘሮ ከዲጃ መሃመድ የቤት እድሳት ከተጀመረላቸው መካከል አንዱ ናቸው፡፡

ልብስ በማጠብ ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ የተናገሩት ወይዘሮ ከዲጃ ፤ ቤታቸው ከፈረሰባቸው ጊዜ ጀምሮ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ተቸግረው መቆየታቸውንና መኖሪያ ቤታቸው እድሳት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል ፡፡

በመረሐግብሩ መሰረት በሐረር ከተማ የቱሪዝም መዳረሻ በሆኑት ጀጎል ግንብ ሙዚየሞች እና በጀጎል ውስጥ የጽዳት ዘመቻ የተካሄደ ሲሆን፤የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እና የአቅመ ደካማ ዜጎች የመኖሪያ ቤት እድሳት ተጀምሯል ፡፡

May be an image of 4 people, people standing and grass

የቱሪዝም ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ፣ የሐረሪ ክልል የካቢኔ አባላትና ነዋሪዎች በስራው ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም