የኢጋድ አባል ሀገራት በቀጣናው የተደቀነውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በጋራ እንዲሰሩ ተጠየቀ

142

ሐምሌ 15/2014 /ኢዜአ/  የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራት በቀጣናው የተደቀነውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋምና በዘላቂነት ለመከላከል በጋራ እንዲሰሩ ተጠየቀ።

8ኛው የኢጋድ የድርቅ አደጋን የመቋቋምና በዘላቂነት መከላከል የግብርና ሚኒስትሮች ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በጉባኤው የኢጋድ አባል ሀገራት ድርቅን ለመቋቋምና በዘላቂነት ለመከላከል እያከናወኑ ስላለው የትግበራ ሂደት ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

በሪፖርቱ በቀጣናው የተከሰተው ድርቅ በበርካታ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ክፉኛ መጉዳቱን የተመለከተ ሲሆን  ለምግብ ዋስትና ችግር መጋለጣቸውንም ጠቅሷል።

የድርቅ አደጋው በተለይም በኬንያ፣ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያደረሰው ጉዳት የምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ፤ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በተደጋጋሚ በድርቅ አደጋ እየተፈተኑ መሆኑን ይገልፃሉ።

በመሆኑም የድርቅ አደጋውን በተናጠል መከላከልም ሆነ መቋቋም ስለማይቻል ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የጋራ ጥረትና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጋር በተያያዘ ድርቅን ለመቋቋም የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተሻለ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የኢጋድ አባል ሀገራትም ፈለጉን በመከትል ለመፍትሄው በጋራ በመስራት የድርቅ አደጋን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችን ለመቋቋም በጋራ መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

የሶማሊያ የግብርና ሚኒስትር መሀመድ አደም፤ በተለያዩ ወቅቶች በሚከሰት ድርቅ አገራት በኢኮኖሚ እየተጎዱ ዜጎቻቸውም ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ በመሆኑ በጋራ ጥረት ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ይገባል ብለዋል።

በቀጣናው የተደቀነውን ከባድ ድርቅ ለመቋቋምና በዘላቂነት ለመከላከል በጋራ መስራት ይገባልም ነው ያሉት።

የኬኒያ ሪፐብሊክ ተወካይ አብዱል ባህሪ ጂሎ፤ በቀጣናው የተደቀነውን ድርቅ ለመቋቋም የጋራ ጥረት ከማድረግ ባለፈ አለም አቀፉ ማህበረሰብም ትከረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

አባል ሀገራቱ ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉም በጉባኤው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም