ዩኒቨርሲቲው የላቀ እውቀትና የመሪነት ሚና ያላቸውን የፖሊስ መኮንኖች የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል- ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

195

ሐምሌ 15 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የላቀ እውቀትና የመሪነት ሚና ያላቸውን የፖሊስ መኮንኖች የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓሉን በተለያዩ መርሃ- ግብሮች በማክበር ላይ ይገኛል።

በመርሐግብሩ ላይ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም በ75 ዓመታት ሂደቱ ከ13 ሺህ በላይ የፖሊስ መኮንኖችን በማፍራት ለተቋም ግንባታና ዘመናዊ የፖሊስ አሰራር የላቀ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፤ የኢትዮጵያን የፖሊስ ሪፎርም በከፍተኛ ደረጃ በማገዝ ላይ ሲሆን ለጎረቤት አገራትም ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

May be an image of 14 people, people sitting, people standing and indoor

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የላቀ እውቀትና የመሪነት ሚና ያላቸውን የፖሊስ መኮንኖች የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በፖሊሳዊ ስነ-ምግባር የታነጹና ቴክኖሎጂን በብቃት መጠቀም የሚችሉ እንዲሁም የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት የተላበሱ አመራሮችን ማፍራት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መስፍን አበበ፤ ዩኒቨርሲቲው ዘመናቸውን የዋጁ በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የሚወጡ መኮንኖችን ከማፍራት አንጻር የማይተካ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

የቅበላ አቅሙ ቀድሞ ከነበረው 150 ሰልጣኞች አሁን ላይ ወደ 3 ሺህ ማደጉን ገልጸው በአውሮፓዊያኑ 2030 ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የመሆን ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የወንጀል ምርመራና ፎረንሲክ ሳይንስ ኮሌጅ መምሪያ ኃላፊና የአውደ-ጥናቱ ተሳታፊ ረዳት ኮሚሽነር ካሳሁን ገብረዮሐንስ፤ ዩኒቨርስቲው ለወንጀል መከላከልም ሆነ ለወንጀል ምርመራ ዘርፍ የጎላ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምርምር ኢንስቲትዩት ኃላፊ ዶክተር ሲሳይ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ለአገሪቷ ሰላምና ደኅንነት ኃላፊነታቸውን በብቃት የሚወጡ የፖሊስ አመራሮችን በማፍራት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖሊስ ከተመሰረተ 80 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን የፖሊስ ዩኒቨርሲቲም ከ1939 ዓ.ም ጀምሮ ዘመናዊ ፖሊስ በማፍራት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም