በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በመኸር እርሻ ከ226ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር ተሸፍኗል

177

ነቀምቴ ሐምሌ 15/2014 /ኢዜአ/ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በመኸር እርሻ 227ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በዞኑ በተያዘው የመኸር ምርት ዘመን እስካሁን ታርሶ ከለሰለሰው 300ሺህ 668 ሄክታር መሬት ውስጥ 227ሺህ ሄክታር የሚጠጋው በተለያዩ የሰብል ዘር መሸፈኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሉሉ ቅጣታ አስታውቀዋል።

በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 115ሺህ 852 ሄክታር በኩታ ገጠም የአስተራረስ  ዘዴ  በሙሉ ፓኬጅ መዘራቱን ኃላፊው አመልክተዋል ፡፡

አርሶ አደሩ በሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ላይ ብቻ  ትኩረት ሳያደርግ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ እንዲጠቀም በተደረገው ጥረት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ መዋሉን አቶ ሉሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለዞኑ ከቀረበው ከ245 ሺህ በላይ ኩንታል ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ከ196 ሺህ ኩንታል የሚበልጠው ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አስረድተዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ዲሪባ በዳሣ በበኩላቸው በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች የዝናብ ስርጭቱ የተስተካከለና ለእርሻ ተስማሚ በመሆኑ በቆሎና ስንዴ በስፋት እየተዘራ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዞኑ ከተላከው ከ8 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎና የስንዴ ምርጥ ዘር ውስጥ አብዛኛው አርሶ አደሩ እጅ መድረሱን ባለሙያው ገልጸዋል።

የሆሮ ወረዳ የኮምቦልቻ ጫንጮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፍርዲሣ በሸና በሰጡት አስተያየት ተስማሚ የዝናብ ስርጭቱ በመጠቀም ካላቸው ሁለት ሄክታር መሬት አንድ ሄክታሩን በጤፍ ዘር የሸፈኑ ሲሆን ቀሪውን ደግሞ ስንዴ ለመዝራት በዝግጅት ላይ መሆናቸው ገልፀዋል፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው መጠቀማቸውን አርሶ አደር ፍርዲሳ ገልጸው በተጨማሪም የፋብሪካ ማዳበሪያ ገዝተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የአካጂ ሰበት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መርጋ ረጋሣ በበኩላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያንና ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ተጠቅመው ሶስት ሄክታር መሬት በቆሎ፣ በኑግ እና ስንዴ ዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ በምርት ዘመኑ 317ሺህ 268 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም