የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አመራሮች ከ600 በላይ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ደገፉ

152

አዳማ፤ ሐምሌ 15/2014 (ኢዜአ)፡ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አመራሮች ለመርቲ ወረዳ ተማሪዎች በ19 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

በድጋፍ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ እንደገለጹት ድጋፉ የበጎ አድራጎት ሥራ ከከተሞች ውጭ በሀገሪቱ ገጠር አካባቢዎች ጭምር ለማስፋፋት ታስቦ የተደረገ ነው።

"በዚህ ክረምት በተለይ የአቅመ ደካሞችን ቤት ገንብተን ለማስረከብ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ገዝተን መማር ለማይችሉ ልጆች ድጋፍ ማድረጋችንና የአረንጓዴ አሻራ ማሳረፋችን ህብረተሰቡ ከኛ ተቀብሎ እንዲያስቀጥል ነው" ብለዋል።

የመተጋገዝና መደጋገፍ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልክት ለማስተላለፍም ድጋፉን ማድረግ ማስፈለጉን  ተናግረዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው በአርሲ ዞን መርቲ ወረዳ አረንጓዴ አሻራ ከማሳረፍ ባለፈ በሚኒስቴሩ አመራሮችና ሰራተኞች አስተዋጽኦ ለ600 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ 20 ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የውሃ መሳቢያ ሞተር ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጀመረውን የበጎ አድራጎት ሥራ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የመርቲ ወረዳ ነዋሪ ሼህ ሃጂ አባስ በበኩላቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አመራሮች  የአቅመ ደካሞችን ቤት ለመገንባትና ተማሪዎች በመማሪያ ቁሳቁስ እጦት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ድጋፍ ማድረጋቸውን አመስግነዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይም ኢዜአ የሀገሪቷን፣ የክልሉን፣ ዞኑንና የወረዳውን ልማትና ዕድገት ለህዝብ በማድረስ ለነበረው አስተዋጽኦ በአርሲ ዞን የመርቲ ህዝብ  ዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም