ለአገር ግንባታ መሰረት ለማኖርና ከመንግስት ለምንፈልገው አገልግሎት የተሟላ ምላሽ ለማግኘት የሚጠበቅብንን ግብር ለመክፈል ተዘጋጅተናል- ግብር ከፋዮች

162

ሐምሌ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአገር ግንባታ መሰረት ለማኖርና ከመንግስት ለምንፈልገው ሁለንተናዊ አገልግሎት የተሟላ ምላሽ ለማግኘት የሚጠበቅብንን ግብር ለመክፈል ተዘጋጅተናል ሲሉ በአዲስ አበባ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈያ ጊዜ በየዓመቱ ከሐምሌ 1 እስከ 30 መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች፤ ለአገራችን እድገትና የመሰረተ ልማት ግንባታ ስኬት የሚጠበቅብንን በመክፈል ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የተጀመሩ የመንገድ ግንባታዎች እንዲጠናቀቁ፣ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎችም አገልግሎቶች እንዲሳለጡ ሁላችንም ግብራችንን በወቅቱ መክፈል ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

በመዲናዋ ከደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች መካከል ወይዘሮ አልማዝ ተክሉ፣ አቶ ክፍሌ አማከለው እና ማትያስ ደነቀ ለአገራችን የውደታ ግደታችን የሆነውን ግብር ለመክፈል ተገኝተናል ብለዋል።

በወቅቱ የሚከፈል ግብር ለአገር ልማት ፈጣን ደራሽ ከመሆኑ ባለፈ ግብር ከፋዮችን ካለ አስፈላጊ እንግልትና ወጭ የሚገላገል መሆኑንም ተናግረዋል።

ግብርን በትክክልና በወቅቱ መክፈል ከመንግስት የሚፈለገውን አገልግፍሎት ሳይጓደል የማግኘትና የመጠየቅ መብትን የሚያጎናፅፍ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሚደርስባት ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ለመላቀቅ በሁሉም ዘርፍ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡

የኢዜአ ሪፖርተር በጉለሌ ክፍለ ከተማ በመገኘት ያነጋገራቸው የወረዳ 08 ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዮናስ ነጋሽ፤ በወረዳው ከ4 ሺህ በላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች 28 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

በ"ቴሌ ብር፣ ሲቢኢ ብር እና ሌሎችም አማራጮች ዜጎች ግብራቸውን በወቅቱ እየከፈሉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም