በክልሉ በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራው መቀጠሉን ፖሊስ አስታወቀ

64
አሶሳ መስከረም 5/2011 በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳና ሌሎች አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራው መቀጠሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የአቤቱታ መቀበል ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ኢንስፔክተር ጌታቸው ጅሬኛ ከሰኔ 16 እስከ 20 / 2010 ዓ.ም. በክልሉ አሶሳ፣ ቶንጎና ሸርቆሌ ከተሞች ግጭት መከሰቱን አስታውሰዋል፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአሶሳ ከተማ ከተጠረጠሩ 97 ሰዎች መካከል 29 መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡ "ከማኦኮሞ ልዩ ወረዳ ቶንጎ 10 ከሸርቆሌ ከተማ ደግሞ 47 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ "ብለዋል፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት የፌደራል ፖሊስ፣ ጠቅላይ አቃቢ ህግና ከሌሎችም የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ምርመራው እየተካሄደ  እንደሚገኝ  አስረድተዋል፡፡ የአሶሳ እና የቶንጎው ጉዳይ አሁንም ምርመራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን የሸርቆሌው ወንጀል ምርመራው ተጠናቆ መዝገቡ ለክልል አቃቢ ህግ መላኩን ጠቁመዋል፡፡ ግጭት ከተከሰተ ሁለት ወራት በላይ መቆጠሩን ያመለከቱት ዋና ኢንስፔክተሩ የዘገየበት ምክንያት ጉዳዩ ውስብስብና ከባድ በመሆኑ ጊዜ በመውሰዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በሚከናወኑ የምርመራ ሥራዎች የሚገኙ ማስረጃዎችን ተከትሎ የተጠርጣሪዎች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊጨምር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ኢንስፔክተር ጌታቸው እንዳሉት የምርመራውን ውጤት በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለአቃቢ ህግ ለማቅረብ እየተሠራ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ  በተደረገ ጥረት የህብረተሰብ እገዛ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ድጋፉን እንዲያጠናክርም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ኢንስፔክተሩ እንዳመለከቱት በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የ15 ሰዎች ህይወት  ሲያልፍ በ104 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፤ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ  የሚገመት ንብረት ጠፍቷል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም