ኦነግ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲሰፍን እንደሚሰራ አስታወቀ

57
አዲስ አበባ መስከረም 5/2011ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲሰፍን ከሁሉም አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ አስታወቀ። የኦነግ አመራር አባላት ዛሬ አዲስ አበባ ሲገቡ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ የግንባሩ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ እንዳስታወቁት፤ "በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ህዝቡ መሪዎቹን በራሱ እንዲመርጥ የታገልንበት የረጅም ጊዜ ግባችን ነው" ብለዋል። በመሆኑም አሁን በአገሪቷ በተፈጠረው መልካም ሁኔታ "ድርጅቱ በዚህ ሂደት ውስጥ ከህዝብ ጋር በመሆን ለውጡን ውጤታማ ለማድረግ ይሰራል" ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ "የህግ የበላይነት ጊዜ ሳይሰጠው ከዛሬ ጀምሮ መከበር አለበት" ያሉት አቶ ዳውድ፤ ለዚህም የለውጡ መሪ ከሆነው መንግስት ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመስራት ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ተናግረዋል። “የእዚህ አገር ፖለቲካ ሰላማዊ እንዲሆን ጠንካራ አቋም ወስደው ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ የመንግሰት መዋቅሮች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ሲሰሩ የቆዩ አመራር አባላት ያደረጉት ትግል ድርጅታችን ወደ አገሩ እንዲገባ ትልቅ መሰረት ሆኖታል። በጥቅሉ አገር ውስጥ ያሉ በውጪም ያሉ የፖለቲካ አካላት እንዲቀራረቡ በማድረጋቸው እኛም እዚህ መጥተናል።የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ነው የመጣው።” በረጅም የትግል ሂደት በእስር ቤት ለተሰቃዩ፣ ለሞቱትና መከራ ለደረሰባቸው ወገኖች ታላቅ ክብር እንዳላቸው የገለጹት አቶ ዳውድ፤ የአሁኑ የአገሪቷ ፖለቲካ በሰላምና በዴሞክራሲ ወደ ፊት እንዲቀጥል ከመንግስት ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በቀጣይ በዓላማ ከሚቀራረቧቸው በአገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከቆዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተጣምረው የህዝቡን ጥቅም ለማስከበር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። “እኛም ወደ ፊት በሰላም ለመንቀሳቀስ ነው የመጣነው። በቀጣይ በዓላማ በምንቀራረባቸው በአገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከቆዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀራርብን እንሰራለን። በዚህ ሂደት ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማረጋገጥና የህግ የበላይነት እንዲከበር እንሰራለን። እንደ ግልም ይሁን እንደ ድርጅት ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ከመንግስት ጋር እንሰራለን።” የድርጅቱ አመራር አባላት ዛሬ ከሰዓት በመስቀል አደባባይ በርካታ ህዝብ ባለበት ደማቅ አቀበባል እየተደረገለት ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም