ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች - ሰርጌ ላቭሮቭ

495

ሐምሌ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነትና ትስስር አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አስታወቁ።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በአፍሪካ ሀገራት የሚያካሂዱትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመልክቶ ባወጡት ጽሁፍ የአፍሪካ ሀገራት በአለም የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚጫወቱት ቁልፍ ሚና እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
ሩሲያም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በወንድማማችነት መርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳላት አውስተው ለአፍሪካ ሕብረት መቋቋምና ሌሎች ክፍለ አህጉራዊ ተቋማት መመስረት ድጋፏ ጠንካራ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የምታካሂደው ግንኙነት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በከፍተኛ ትኩረት የምታየውና ልዩ ቦታ የምትሰጠው ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
“አፍሪካውያን ለሩሲያ የክፉ ቀን ደራሽ ናቸው” ሲሉ ያስታወቁት ላቭሮቭ፤ ሩሲያ በአለም አቀፍ መርሆዎች መሠረት ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነቱ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በዩክሬን ጦርነትና በኮቪድ-19 ምክንያት የተከሰቱ አለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቋቋም ሩሲያ ወደ አፍሪካ ሀገራት የምትልከውን የምግብ፣ የምርጥ ዘር፣ የሃልይና ሌሎች አቅርቦቶችን እንደምታጠናክር አመልክተዋል።
እ.አ.አ በ2019 ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ የተወሰነውን ስትራቴጂክ ስምምነትም በላቀ ሁኔታ ለማሳደግ ሩሲያ ትሰራለች ብለዋል ላቭሮቭ።
ሩሲያ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርኋ አፍሪካውያን የውስጥ ችግራቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ ሉዐላዊነታቸውን በጠበቀ መልኩ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረው፤ ለአፍሪካ የልማት አጀንዳ መሳካትም ያለሰላሠ ድጋፏን ታጠናክራለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም