የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው

131

ሐምሌ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ የምስረታ በዓሉን ዛሬ በማክበር ላይ ይገኛል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊት ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ጨምሮን የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖሊስ ከተመሰረተ 80 ዓመት እንደሞላውና የፖሊስ ዩኒቨርስቲውም ከተመሰረተበት 1939 ዓ.ም አንስቶ ዘመናዊ ፖሊስን የመገንባት ኃላፊነት እየተወጣ ነው ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራሉ።

ዩኒቨርስቲው በጀግንነት መጠበቅ፣ በሰብዓዊነት ማገልገል የሚል መሪ ሃሳብን በማንገብ ለፖሊስ ሰራዊት ዕድገትና መሻሻል አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ገልጸዋል።

ሆኖም ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ማደግ ባለበት መጠን ሳያድግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜም ዩኒቨርስቲው ዘመኑን በዋጀ መልኩ ጠንካራ የፖሊስ አመራርና ሰራዊት አባላትን እንዲያፈራ ተደርጎ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማደጉን ነው ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ያብራሩት።

ዩኒቨርሲቲው ኃላፊነታቸውን በብቃት የሚወጡ ጠንካራ የፖሊስ ሰራዊትን ለማፍራት መትጋት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው የዩኒቨርስቲው የቅበላ አቅም ቀድሞ ከነበረው 150 ሰልጣኝ አሁን ላይ ወደ 3 ሺህ ማደጉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰአት የዩኒቨርስቲውን የ75ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የተመለከተ ውይይት እየተካሄደ ሲሆን የአውደ ርዕይ ጉብኝትና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ይከናወናል።

የቀድሞው የአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ በ2030 ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የፖሊስ ዩኒቨርስቲ የመሆን ራዕይ ይዟል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም