በቆላማ አካባቢዎች የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በአካባቢዎቹ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት-ኢንጅነር አይሻ ሙሐመድ

90

አዳማ ሐምሌ 15 ቀን 2014(ኢዜአ) በቆላማ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋምና በቂ የመስኖ ውሃ ለማግኘት በአካባቢው የሚካሄደው ችግኝ ተከላ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ ሙሐመድ አሳሰቡ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ማዕከል አስተባባሪና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ ሙሐመድ በአርሲ ዞን አርባጉጉ መርቲ ወረዳ በመገኘት የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ ሙሐመድ በዚህ ወቅት በቆላ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋምና በቂ የመስኖ ውሃ እንድናገኝ የችግኝ ተከላውን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል ።
በዚህም ከ20ሺህ በላይ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ኢንጅነር አይሻ ገልጿል ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ማዕከል አስተባባሪ ዶከተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ የሀገራችንን ሁሉን አቀፍ ቀጣይ ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል ።
በተለይ መርቲ ወረዳ የደን ልማቱ በሰው ሰራሽ ችግር የሳሳበት በመሆኑ ህብረተሰቡ የችግኝ ተከላውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል ።
በወረዳው ሸሞ ጋዶ ቀበሌ ያየነው ከንኪክ ነፃ ቦታ ላይ የለማው ደን ትልቅ ምሳሌና ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው የአካባቢው ህብረተሰብ ይሄን ተሞክሮ በሁሉም ቀበሌዎችና ወረዳዎች ማስፋፋት ይኖርበታል ነው ያሉት ።
ኢትዮጵያን በአረንጓዴ የማልበስ ግባችንን በሁሉም የተቀናጀ ርብርብ እውን እናደርጋለንም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም