ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል ያለጸጥታ ሥጋት እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል-ፖሊስ

216

ሐዋሳ፤ ሐምሌ 14/2014 (ኢዜአ)፡ ሐምሌ 19 የሚከበረው የሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የሐዋሳ ከተማ አስተዳድር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረሰ ቡሳሮ ለኢዜአ እንደገለጹት ሐምሌ 19 የሚከበረው ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል በዓል በሠላም እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ለበዓሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶች ያማረ ቆይታ አድርገው እስኪመለሱ ድረስ ያለ አንዳች የጸጥታ ሥጋት እንዲንቀሳቀሱ ከወትሮው የተለየ የሠላምና ደህንነት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

የከተማው ፖሊስ ከሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የጋራ ዕቅድ አውጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ከደንብ አስከባሪዎች፣ ከጫኝና አውራጆች፣ ከሆቴል ባለቤቶች፣ ከወጣቶችና ሌሎች በየክፍለ ከተማው ካሉ ማህበራዊ አደረጃጀቶች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸው፤ ''ህብረተሰቡ የሠላሙ ባለቤት ራሱ መሆኑን ተገንዝቦ አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ነው ብለዋል ፡፡

በተለይ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለ ዋጋ ጭማሪ እንግዶቻቸውን ከማስተናገድ ባለፈ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከቱ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ የጋራ መግባባት መፈጠሩን ተናግረዋል ፡፡

በበዓሉ ዕለት በቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ የተሸከርካሪ መጨናነቅ እንዳይፈጠርና ለጸጥታ ሥራው ምቹ እንዲሆን ዝግ የሚደረጉ መንገዶች መኖራቸውን ጠቁመዋል ፡፡

በመሆኑም ከሱሙዳ አደባባይ እስከ ዋርካ ሆቴል፣ ከሱሙዳ አደባባይ እስከ ትሩፋት መብራት፣ ከሱሙዳ አደባባይ የፒያሳና የጤና ቢሮ መስመሮች እንዲሁም ከብሉናይል እስከ ፌነት ክትፎ ቤት ድረስ ያሉ መንገዶች ከዋዜማው አሥር ሰዓት ጀምሮ ለተከርካሪዎች ዝግ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።

እንግዶች ተሸከርካሪዎቻቸውን ምቹ በሆነ ቦታ ማቆም እንዲችሉም ከቤተ ክርስቲያኑ ጎን በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ትምህርት ቤት፣ ታቦር ትምህርት ቤትና በመስቀል አደባባይ ግቢ ውስጥ በቂ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ መዘጋጀቱን ገልጸዋል ፡፡

በዕለቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶች አፋጣኝ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜያዊ ምድብ ችሎት ሁሉም የፍትሕ አካላት የሚገኙበት  ከቤተክርስቲያኑ አቅራቢ እንደሚቋቋምም አስረድተዋል።

እንግዶችም ሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የፀጥታ አካላትን እገዛ ለማግኘትና ጥቆማ ለመስጠት በ 046-220- 1046፣ 091 658 6115 እና በ 091 899 8000 በመደወል ማሳወቅ እንደሚችሉም ጠቁመዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም